የኮለምበስ መታሰቢያ ቀን

“እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 12, 1492 ዓም በክሪስቶፈር ኮሎምበስ የተመሩ ሦስት የስፓኝ መርከቦች ዛሬ ባሃማስ ተብላ ከምትጠራው ደሴት ላይ መልህቃቸውን ጣሉ።” ሲል ይንደረደራል የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ።

“በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ የኮሎምበስ ቀን ተብሎ የሚከበረውም ይህ ቀን የዚያች ዕለት መታሰቢያ ነው። ክስተቱ የኮሎምቢያ ግብይት ወይም ልውውጥ በመባል ለሚታወቀው ዓለምን የቀየረ መጠነ ሰፊ፣ ዓለም አቀፍ የምግብ፣ የእንስሳት፣ የዕፅዋት፣ የሕዝብ ልውውጥ እና በሽታዎች ጭምር የሚመዛመቱበት ዓለም አቀፍ ግንኙነት የተጀመረበትም ቀን ነው።

በዚህም የተነሳ፣ 1492 ዓም በብዙ የታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ በዘመናዊው የዓለም ታሪክ የተለየ ሥፍራ የሚሰጠው ዓመት ተደረጎ ይቆጠራል።” በኮለምበስ መታሰቢያ ቀን ላይ ትኩረት ያደረገው የዕለቱ-ርዕሰ አንቀጽ ይቀጥላል።

የዓለም ህዝብ ከ1492 ወዲህ ከአራት እጥፍ በላይ ጨምሯል። በ1650 እና በ1850 በነበረው ጊዜ ብቻ በእጥፍ ነው የጨመረው።

“ምንም እንኳን ሌሎች በርካታ ተጨማሪ ምክንያቶች ለተከተለው ግዙፍ እድገት አስተዋፅዖ ቢያደረጉም፤ ዋነኛው ግን መጠኑ በእጅጉየጨመረው እና የተሻሻለው የምግብ አቅርቦት ነው።

በጊዜው በዛሬዋ አሜሪካ ይኖሩ የነበሩት ነባር ሕዝቦች በነበራቸው የምግብ አቅርቦት ላይ የተጨመሩት እንደ በቆሎ፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ለውዝ ወይም ኦቾሎኒ፣ ቃዛፋ፣ አናናስ፣ በርበሬ እና ኮካዋ የመሰሳሉት አትክልት እና የሰብል ዓይነቶች የተለየ ዋጋ ያላቸው ናቸው።” ያለው የዕለቱ-ርዕሰ አንቀጽ በመቀጠልም፤ “ድንች በጊዜው በመካከለኛው እና በሰሜናዊ አውሮፓ ለሚኖሩ ድሃ የማሕበረሰብ ክፍሎች በጣም አስፈላጊው የምግብ ምንጭ መሆን ሲጀምር፤ በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በአፍሪካ የተዋወቁት በቆሎ እና ቃዛፋም ከዚያ ቀደም በአህጉሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይታወቁ የነበሩትን የሰብል ዓይነቶች በመተካት የዘወትር ምግብ መሆን መጀመራቸውን ይዘረዝራል።

በቻይናም በተለይ እንደ ድንች፣ በቆሎ እና ኦቾሎኒ የመሳሰሉትን የአዲሱ ዓለም የምግብ ሰብሎች መተዋወቅ ከ1500 እስከ 1650 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ የዚያች አገር ሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ምክኒያት ሆኗል” ሲል ርዕሰ አንቀጹ ያስረዳል።

አዳዲስ ምግቦችን ወደ ሁሉም የዓለም ማዕዘናት ያስተዋወቀው የኮሎምቢያ ልውውጥ የተሰኘው ይህ ክስተት ዓለም አቀፋዊ ነበር።

ከ1492ዓም በፊት በፍሎሪዳ ክፍለ ግዛት ብርቱካን አልነበረም። በኢኳዶር ሙዝ፣ በሃንጋሪ ደግሞ በርበሬ ተፈጭቶ የሚሠራው የፓፕሪካ ቅመም አልነበሩም።