"የዓለም የአየር ሙቀት ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማያውቅ መጠን እንደጨመረ የዓለም የሜቴዎሮሎጂ ድርጅት አስታውቋል" በማለት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግብፅ ሻርም ኤል ሼክ ውስጥ በተካሄደው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ-27) ላይ የተናገሩትን በመጥቀስ የዛሬው ርዕሰ አንቀፅ ፅሁፉን ይጀምራል።
"ዩናይትድ ስቴትስ በሀገር ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ካሁን ቀደም ታይቶ የማያውቅ ሥራ አከናውናለች" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣
"ዛሬ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት፣ እዚህ ቆሜ ዩናይትድ ስቴትስ የ2030 ዓመተ ምህረት የበካይ ጋዝ ቅነሳ ግቧን እንደምታሳካ በዕርግጠኝነት አስታውቃለሁ" ብለዋል።
የሆነ ሆኖ አለ ርዕሰ አንቀፁ በማስከተል በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት በይበልጥ እየተጎዱ ያሉት ለቀውሱ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ከጉዳቱ ለማገገም አቅም የሌላቸው ሀገሮች እና ማኅበረሰቦች ናቸው።
በአብዛኛው ደግሞ የቀውሱ ዋነኞቹ ምክንያቶች እነርሱ አይደሉም ካለ በኋላ ርዕሰ አንቀፁ "ለዚህም ነው ፕሬዚዳንት ባይደን ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ ለሆኑ ጥረቶች ለውጡን ለመላመድ የሚከናወኑ ሥራዎችን ጨምሮ ለመደገፍ ዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ 11 ቢሊዮን ዶላር እንደምትሰጥ ይፋ ያደረጉት" በማለት አስረድቷል።
በእንግሊዝኛ የአህጽሮት ስሙ "ፕሪፔር" ተብሎ የሚጠራው ይህ የፕሬዚዳንቱ የአየር ንብረት ለውጥን መላመድ እና መቋቋም አስቸኳይ ዕቅድ በታዳጊ ሀገሮች የሚኖሩ ቁጥራቸው ከግማሽ ቢሊዮን የሚበልጥ ሰዎችን ለአየር ንብረት ለውጦች ምላሽ ለመስጠት እንዲችሉ ለመርዳት መሆኑን አመልክቷል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተናገሩትንም ርዕሰ አንቀፁ ይጠቅሳል።
"ቅድሚያ ክፍያ ይሆን ዘንድ ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምንሰጥ እናስታውቃለን። እርሱም በተለይ በመላ አፍሪካ "ፕሪፔር" የአየር ንብረት ለውጥ መላመድ ዙሪያ የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለሚያግዙ መርኃ ግብሮች የሚውል ነው። ይህም ዩናይትድ ስቴትስ እና ግብጽ በሰኔ ወር የጀመሩትን መርኃ ግብርም ይጨምራል" ሲሉ ፕሬዚዳንት ባይደን አስታውቀዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ከሌሎች መርኃ ግብሮች በተጨማሪ "ግሎባል ሺልድ" በሚል የእንግሊዝኛ ስም ለሚጠራው እና የቡድን-7 አባል ሀገሮች የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትለው ጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ሀገሮችን ለመርዳት ላዘጋጁት መርኃ ግብርም ድጋፍ በመስጠት ላይ ትገኛለች። ሌላው የቡድን -7 መርኃ ግብር የሆነው ደግሞ የዓለም አቀፍ መሠረተ ልማት እና ኢንቬስትመንት አጋርነት ነው።
ባለዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ሀገሮች ላሏቸው የመሠረተ ልማት ፍላጎቶች የአየር ንብረት ጉዳይ ባገናዘበ መንገድ ለመድረስ የታለመ ሲሆን ይህንንም መርኃ ግብር ዩናይትድ ስቴትስ እየደገፈች መሆኗን ርዕሰ አንቀፁ አውስቷል። አስከትሎም ፕሬዚዳንት ባይደን የተናገሩትን ጠቅሷል።
"ከአንድ መቶ ሠላሳ የሚበልጡ ሀገሮች ከዓለም ዙሪያ ከሚወጣው ከጠቅላላው የሜቴን ጋዝ ልቀት ከግማሽ የሚበልጠውን ለመቀነስ ፈርመዋል። ሜቲይን ከካርቦን በ80 እጥፍ የሚበልጥ ጥንካሬ አለው፥ አሁን እያየነው ካለው አየር ግለት ውስጥ ከግማሽ ለሚበልጠው ምክንያቱ ሜቴይን ነው። ስለዚህ የሜቴይንን ልቀት እስከ 2030 ዓ/ም ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ በ30 ከመቶ ለመቀነስ ከቻልን የ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሲየስ ግባችንን የማሳካት ዕድል ይኖረናል" ብለዋል።
"ወሳኝ በሆነው በዚህ አሰርት ባሉት ዓመታት ሁላችንም ጥረታችንን ማፋጠን አለብን። የተደቀነብን ፈተና ግዙፍ ነው። ቢሆንም እኛ ከተደቀነው ፈተና የበለጠ አቅም አለን። ያን ፈፅሞ መጠራጠር የለብንም" ሲሉ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተናገሩትን ጠቅሶ ርዕሰ አንቀፁ ፅሁፉን አጠቃልሏል።