የጆ ባይደን አስተዳደር የሰብአዊ መብት መጠበቅ አለበት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መወደሰ አለባቸው፣ ሰብአዊ መብትን የሚረግጡት ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብሎ እንደሚያምን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ካውንስል ፊት ቀርበው ተናግረዋል ሲል፣ የዕለቱ ርዕሰ-አንቀጽ፣ ሀተታውን ጀምሯል።
ሁሉን አቀፍ በሆኑት የሰብአዊ መብት ህጎች መሰረት፣ ሁሉም መብቶች ሁለንተናዊ፣ የማይነጣጠሉ፣ የተሳሰሩና የተያያዙ ናቸው ይላሉ ብሊንከን።
“ዩናይትድ ስቴትስ ዲሞክራሲንና ሰብአዊ መብትን የውጭ ፖሊሲያችን ምስሶ አድርጋ ታስቀምጣለች። ምክንያቱም ለሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ናቸዋና። ባለን ተመክሮ መሰረት ዲሞክራሲ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ምን ጊዜም ቢሆን አካታች፣ አክባሪና ነጻ ሀገር እንዲኖር ለማድረግ የሚጥር በመሆኑ ጽኑ መሰረት አለው።”
ዩናይተድ ስቴትስ እአአ ከ2022 እስከ 2024 በሚኖረው ጊዜ ውስጥ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የሰብአዊ መብት ካውንስል፣ መቀመጫ ለማግኘት ለምርጫ ለመወዳደር ካቀደችባቸው ዋና ምክንያቶች አንዱ ነው ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
“የሰብአዊው መብት ካውንስል አባልነት በሰብአዊ መብት አከባበር ላይ የከፈተኛ ደረጃ መለኪያ የሚያንጸባርቅ መሆኑን በማረጋገጥ ላይ እናተኩራለን። መጥፎ የሰብአዊ መብት አያያዝ ያላቸው ሀገሮች የሰብአዊው መብት ካውንስል አባላት መሆን የለባቸውም። ካውንስሉ በአለም ዙርያ የሰዎች መብቶች እንዲከበሩ በበለጠ ለመስራት እንዲችል የካውንስሉን አባልነትና ስራ ለማሻሻል ተባብረን መስራት ይኖርብናል።”
ብዙ የካውንስሉ አባል ሀገሮች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተመሰረተበትን እሴት ለማሰናከል የሚሰሩት ሳይቀሩ፣ የሰብአዊ መብት መከበርን ያሞግሳሉ። “ማንኛችንም እንደግለሰቦች ሰብአዊ መብታችን የመከበር መብት አለን። መንግስታትም እነዚህን መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶችን፣ የማክበር ግዴታ አለባቸው” ሲሉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን አስገንዝበዋል።
“የኢኮኖሚ ልማትን በማራመድ ሰበብ ሰብአዊ መብትን የማያከብሩት ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ቬነዝዌላን፣ ኒካራግዋን፣ ኩባንና ኢራንን በመሳሰሉት ሀገሮች የሚፈጸሙትን በደሎች ማንሳታችንን እንቀጥላለን። የሩስያ መንግስት አለክሰይ ኔቫልኒን ካለምንም ቅድመ-ግዴታ አሁኑኑ ከእስር እንዲፈታ የምናደርገውን ጥሪ እንደግማለን። መብታቸውን በመተግበራቸው ምክንያት የታሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሩስያውያንም እንዲፈቱ መጠየቃችን ይቀጥላል። ሺንዢያንግ ቻይና ውስጥ የጭካኔ ተግባሮች ሲፈጸሙ ወይም ደግሞ ሆንግ ኮንግ ላይ መሰረታዊ ነጻነቶች ሲረገጡ ሁሉን አቀፍ መብቶች እንዲከበሩ መናገራችን አይቀርም።”
“ዩናይትድ ስቴትስ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲዳብሩ ለመስራት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ናት” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን።
አያይዘውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የሰብአዊው መብት ካውንስል፣ በተሰጠው ውክልና መሰረት እንዲሰራና በአለም ዙርያ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማድረጉን ለማረጋገጥ፣ በዚህ አካል ካሉት ወዳጆችና አጋሮች ጋር ተባብረን ለመስራት በጉጉት እንጠብቃለን” ማለታቸውን ጠቅሶ፣ የእለቱ አዕሰ-አንቀጽ ሃተታውን አብቅቷል።