የ2021 ዓ.ም. የፕሬዚዳንቶች ቀን

በወርኃ ፌብርዩዋሪ ሦስተኛ ሰኞ አሜሪካዊያን በሚያከብሩት የፕሬዚዳንቶች ቀን ያለፉ መሪዎቻቸውን በክብር ይዘክራሉ። ቀኑ መከበር የጀመረው የዩናይትድ ስቴትስን የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሺንግተንን ዘወትር ለማስታወስ በሚል ሃሣብ ነበር።

ጆርጅ ዋሺንግተን በአሜሪካ አብዮታዊ ጦርነት ውስጥ የሰጡት ጉልህ አመራርና የሃገሪቱ የመጀመሪያው መሪም መሆናቸው በህዝብ ዘንድ እጅግ የሰፋ ተወዳጅነትን እንዳተረፈላቸው ለፕሬዝዳንቶች ቀን የወጣው የዛሬው ርዕሰ አንቀፅ ይናገራል። “እናም የዩናይትድ ስቴትስ አባት እየተባሉ ሲጠሩ ኖረዋል፤ ዛሬም እንደዚያው ይጠራሉ። ይህ የሆነው በወቅቱ እጅግ ኃያል በነበረው ጦር ላይ የአሜሪካ ቅኞችን ኃይሎች መርተው ለድል በማብቃታቸው ነው” ሲል ይቀጥላል።

ዋሺንግተን ከእርሳቸው በኋላ የተነሱ ፕሬዚዳቶች ሁሉ የተከተሉትን የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን አካሄድ ቅርፅ በማስያዝ አርአያ መሆናቸውን ርዕሰ አንቀፁ ያስታውሳል።

የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችለውን ያህል በቂ ችሎታና አቅም ሊኖረው እንደሚገባ ቢያምኑም የንጉሠ ነገሥትን ያህል ፈላጭ ቆራጭ መሆን እንደሌለበት ግን አስተውለዋል።

ምናልባት ሥልጣን ላይ እያሉ ቢያልፉ ሰዉ ‘የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን የዕድሜ ልክ ሹመት ነው’ ብሎ እንዳያስብም በመሥጋት ዋሺንግተን ሁለት የምርጫ ዘመኖችን ካገለገሉ በኋላ ሥልጣናቸውን በፍቃዳቸው ለቀቁ።

ከዚያ በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለአራት የምርጫ ዘመናት ከዘለቁት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዘቬልት በስተቀር ከሁለት ዘመናት በላይ ያገለገለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የለም። በ1943 ዓ.ም. (በኢት.የዘ.አ.) የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው የህገ መንግሥቱ 22ኛ ማሻሻያ የፕሬዚዳንቱ አገልግሎት ከሁለት ዘመናት እንዳይበልጥ በህግ ደነገገ።

የፖለቲካ ሥልጣንን፣ ወታደራዊ እንቅስቃሴንና የምጣኔ ኃብት ፖሊሲን ጨምሮ ፕሬዚዳንት ዋሺንግተን የዩናይትድ ስቴትስን መጭ መንገድ የቀረፁት የጎላ ተፅዕኖ ባሳደረ ሁኔታ መሆኑንም ርዕሰ አንቀፁ ይናገራል።

በዚህም ምክንያት ፕሬዚዳንት ዋሺንግተን ባረፉ በዓመቱ አንስቶ የልደታቸው ቀን ይፋ ባልሆነ ሁኔታ እራሳቸው በቀለሷት አዲስ ሃገር ውስጥ መከበር መጀምሩን ርዕሰ አንቀፁ አስታውሶ ዕለቱ በኦፊሴል በዓል እንዲሆን የዛሬ 36 ዓመት መወሰኑን ገልጿል። ከዚያ በኋላ አሜሪካዊያን የካቲት 5 የተወለዱትን ሌላኛውን ታላቅ መሪ የአብርሃም ሊንከንንም ልደት ማክበር ጀመሩና የአውሮፓው ፌብርዩዋሪ ሦስተኛ ሣምንት የሁሉም ፕሬዚዳንቶች ክብር ቀን ሆነ።

“በዚህ የፕሬዚዳንቶች ቀን አሜሪካዊያን በበጎና በክፉ ቀናት ሁሉ እጅግ ብርቱና የጅብዱ ሥራ የሚጠይቀውን አመራር ስለሰጧቸው ፕሬዚዳንቶቻቸው ክብርና ሰላም እንዲሆን ይሻሉ” ይላል ርዕሰ አንቀፁ በማጠቃለያው።