ወረርሽን የማጥፋት ጉዞ

“ፖይሎማይልትስ እየተባለ የሚጠራው ፖሊዮ፣ ወይም የልጅምነት ልምሻ፣ ሽባ የሚያደርግና አደገኛ በሆነው የፖሊዮ ቫይረስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው” ይላል የእለቱ ርእሰ አንቀጽ ጽሁፉን ሲጀምር፡፡ የፖልዮ ቫይረስ የነርቭን ማዕከላዊ ስርዓት በመውረር፤ በሰዓታት ውስጥ ሽባ ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡ በየትኛውም እድሜ ክልል ያሉትን ሰዎች ቢያጠቃም፣ በተለይ ከአምስት ዓመት ዓመት በታች ያሉት ህጻናት ግን፣ በቀላሉ ሊጠቁ እንደሚችሉ፣ ርእሰ አንቀጹ ያስረዳል፡፡ ፖሊዮን በክትባት መከላከል የሚቻል ቢሆንም፣ አንዴ የተለከፈው ሰው ግን፣ ሊድን የሚችልበት መንገድ የለም ብሏል ርእሰ አንቀጹ፡፡

በ125 አገሮች፣ ከ350 ሺ በላይ የሆኑት ህጻናትን ሽባ ያደረገውን ፖሊዮ፣ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት፣ እኤአ በ1988፣ የዓለም የጤና ጉባኤ ፣ ቃል የገባ መሆኑንም ርእሰ አንቀጹ አስታውሷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የእርዳታ ድርጅት ዩኤስኤድ፣ አደገኛ የሆነውን ፖሊዮ ከአሜሪካ፣ እኤአ በ1994፣ ከምዕራባዊ ፓስፊክ ደግሞ በ2000 ዓመተ ምህረት፣ እንዲሁም ከደቡብ ምስራቅ ኤዥያ በ2014፣ በቅርቡም በዚህ ዓመት ከአፍሪካ እንዲጠፋ በማድረግ ረገድ፣ ከፍተኛ ድርሻ መጫወቱን ርእሰ አንቀጹ አስታውቋል፡፡ በአራት ዓመታት ውስጥ፣ በአህጉሪቱ ምንም ዓይነት የፖሊዮ ቫየረሰ ባለመታየቱ፣ በዚህ ዓመት፣ የነሀሴ ወር አጋማሽ ላይ፣ አፍሪካ ከፖሊዮ ነጻ የወጣችበትን ሰርትፊኬት መቀበሏንም ርእሰ አንቀጹ ገልጿል፡፡ የመጨረሻዋ አገር የነበረችው ናይጄሪያ፣ በጣም ጥብቅ የነበረውን መስፈርት አሟልታ፣ በአፍሪካ ካሉ 46 አገሮች ጋር በመቀላቀል፣ በጤናው ዓለም ታሪካዊ የሆነውን እለት ያበሰረች አገር ሆናለች ብሏል፡፡

ዛሬ ፖሊዮ፣ 99.9 በመቶ መቀነሱን የገለጸው ርእሰ አንቀጽ፣ አፍጋኒስታንና ፓኪስታን ብቻ በተወሰነ መልኩ ፣ አሁንም በበሽታው ተጋልጠው የሚገኙበት ሁኔታ መኖሩን አስታውቋል፡፡

ርዕሰ አንቀጹ በመቀጠል፣ “በአብዛኞቹ አገሮች፣ ፖሊዮን ለማጥፋት የሚጓዙበት መንገድ ቀላል አይደለም፡፡ የተራዘመው ግጭት፣ የተዛባው የኢንፎርሜሽን ስርጭት፣ የሚፈቀናለው ህዝብ፣ ተራርቆ ያለው ማህበረሰብና ሌሎች በርካታ ፈተናዎች ሂደቱን የገቱ ሲሆን፣ አሁንም ቫይረሱን ለመዋጋት የሚደረገውን ሂደት እያስተጓጎሉ መሆኑን” አስገንዝቧል፡፡ “ይህም ሆኖ የቫይረሱ ስርጭት እንዲቆም ከተፈለገ፣ ቀጣይነት ያለውና እየተሻሻለ የሚሄደው ምላሽ መቀጠል አለበት፡፡ ይህ የሚሆነው በማያወላውል ቁርጠኝነት፣ ችግሮችን በዘዴ እየፈቱ፣ የማህበረሰቡ አባላትና ፣ የየአገራቱ መንግሥታና ዓለም አቀፍ አጋሮች በሚሰሩት ጠንካራ ሥራ፣ ከፖሊዮ ነጻ የሆነ ዓለምን መፍጠር ተችሏል፡፡” ብሏል የርእሰ አንቀጹ ጽሁፍ፡፡

ሥፍር ቁጥር ከሌላቸው እነዚህ የጤና ሠራተራኞች ጋር፣ ከማህበረሰብ መሪዎችና እንዲሁም አንድም ወደ ኋላ ቀርቶ ያመለጣቸው ህጻን እንዳይኖር እያንዳንዱን ለይተው ከሚከታተሉት በጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበር የዩናይትድ ስቴትስ የእርዳታ ድርጅት፣ ፖሊዮን ከመላው ዓለም ለማጥፋት በተደረገው ጥረት፣ በየዓመቱ ከ400ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናትን ማስከትብ መቻሉን ርእሰ አንቀጹ አስረድቷል፡፡ ዛሬ ሽባ ከመሆን ተርፈው ተራምደው መሄድ የቻሉ 19 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ሲኖሩ ከ 1.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በፖሊዮ ከመሞት ድነው በህይወት መኖር መቻላቸውንም ርእሰ አንቀጹ አስታውቋል፡፡

በዚህ የ2020 ዓመት፣ የዓለም የፖሊዮ ቀን ሲከበር፣ የተለየ የሚያደርገው፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎትም ሆነ የዘወትር መከላከያ ክትባቶችን እንኳ መስጠት ከባድ በሆነበት፣ በዚህ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት፣ አፍሪካ ከፖሊዮ ነጻ የወጣችበትን ሰርትፊኬት ማግኝቷ ነው፣ ብሏል ርእሰ አንቀጹ፡፡

በመጨረሻም፣ “የዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ ድርጅት ወይም ዩኤስኤድ እና አጋሮቹ፣ የተገኘውን ልምድ መሠረት በማድረግና፣ ፖሊዮን ለማጥፋት የተዘረጋውን መሠረተ ልማት በመጠቀም፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን ወረርሽኝም ሆነ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉትን ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል፣ አቅደዋል፡፡” በማለት ርእሰ አንቀጹ ሀተታውን ደምድሟል፡፡