ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት የተነሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአጣዳፊ የምግብ ዋስትና ችግር እንዲሁም ለበረታ ረሃብ መጋለጣቸው ቀጥሏል። በሰላምም ጊዜ ቢሆን ለሦስት ዓመታት በተከታታይ በደረሰው የከበደ ድርቅ እና በቂ ምርት ባለመገኘቱ የተነሳ በከባዱ በተጠቁት አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ የምግብ እርዳታ የሚጠብቅ ነው። ሆኖም የፌዴራል እና የክልል ኃይሎች እና የትግራይ ህዝባዊ ነጻ አውጪ ግንባር ህወሓት ውጊያ አስቀድሞም አስከፊ የነበረውን ችግር አባብሶ ወደ ሰብዐዊ አደጋነት አሸጋግሮታል በማለት የዛሬ ርዕሰ አንቀፅ ፅሁፉን ጀምሯል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሰረት ከአምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮኑ የትግራይ ህዝብ ውስጥ ከዘጠና ከመቶ የሚበልጡት አጣዳፊ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ርዕሰ አንቀፁ አውስቷል።
ዩናይትድ ስቴትስ ባለፉት ቅርብ ሳምንታት በኢትዮጲያ መንግሥት እና በትግራይ እና የአፋር ክልሎች ባለሥልጣናት በተወሰዱት ርምጃዎች የተበረታታችው በዚህ ምክንያት ነው። እርምጃዎቹ ግጭቱን እንዲያከትም መሰረት የጣሉ እና በጦርነት ለተጎዱት ማህበረሰቦች አጣዳፊ የምግብ እርዳታ ለማድረስ ያስቻሉ ርምጃዎች በመሆናቸው ነው በማለት ርዕሰ አንቀጹ ይቀጥላል።
ለምሳሌ አለ በማስከተል ለምሳሌም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አንስተዋል። አንዳንድ የፖለቲካ እስረኞችን እና ሌሎችም ታሳሪዎች ለቅቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በየበኩላቸው ተኩስ አቁም አውጀዋል ካለ በኋላ የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው አብዛኞቹን ኃይሎቻቸውን ከአፋር ክልል ያስወጡ ሲሆን ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኞች መሆናቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል ብሏል።
ያ እንዳለ ሆኖ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን "ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እንዳሉት በዚህ ግጭት ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሰብዐዊ ርዳታ ባስቸኳይ ቀጣይነት ባለው እና ባልተገደበ መንገድ እንዲደርስ ወገኖቹ ጥረቶቻቸውን አፋጥነው እና ሰፋ እድርገው እንዲቀጥሉ" ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን አውስቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንክን አክለው ወገኖቹ ይህን ዕድል አስፈላጊውን የጸጥታ አጠባበቅ ስርዓትን ባካተተ መንገድ በድርድር ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ለትግራይ ክልል መሰረታዊ አገልግሎቶች በአስቸኳይ እንዲቀጠሉ ለማድረግ እንዲጠቀሙበት ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ለዚህ ህይወት አድን ጥረት ድጋፏን ለመቀጠል ዝግጁ ነች፥ አንድነቷ ለተጠበቀ ለበለጸገች እና ሉዐላዊት ኢትዮጵያ ባላት ቁርጠኝነት ትቀጥላለች፤ በሀገሪቱ ላሉት ክፍፍሎች መፍትሄ ለሚያመጣ እና ለሁሉም ለኢትዮጵያውያን ሰላም እና ጸጥታን ለሚያሰፍን አሳታፊ የፖለቲካ ሂደት ድጋፍዋን መስጠቷን ትቀጥላለች በማለት ርዕሰ አንቀፁ ሃተታውን አጠቃሏል።