Accessibility links

Breaking News

ለውጤታማ የጸረ-ሽብር ዘመቻ የሴቶች አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው


ፎቶ ፋይል፦ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ አአ ሚያዚያ 24, 2023, በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት
ፎቶ ፋይል፦ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ አአ ሚያዚያ 24, 2023, በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት

በመላው ዓለም የአደገኛ አክራሪዎች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል። ይህ የአክራሪዎቹ እንቅስቃሴም በሴቶችና የሴቶች መብት ላይ ያነጣጠረ እና እየጨመረ የመጣ ችግር እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ ድርጅት ያስታውቃል። አሸባሪዎች ጾታዊ እና ጾታን መሠረት ያደርጉ የጥቃት ዘመቻዎችን በማሕበረሰቡ ውስጥ ይፈጽማሉ፣ ይህም ነዋሪዎችን ሲያሸብር የማኅበራዊ ትስስሩንም ይበጣጥሰዋል ሲል የዛሬው ርዕሰ-አንቀጽ ሃተታውን ይጀምራል።

በዚህም ምክንያት ሴቶች ዘወትር የሽብር ሰለባዎች ብቻ ተደርገው ይታያሉ። እውነታው ግን፣ የአክራሪዎች ጥቃትን ለመከላከልም ሆነ ለጥቃቱ ለሚሰጠው ምላሽ ወሳኝ ድርሻ አላቸው። “ሴቶች እና ልጃገረዶች በሰላም ድርድር፣ ርዳታን በማዳረስ፣ ማኅበረሰባቸውን በማገዝ ረገድ ከፊት ተርታ ተሰልፈው ይገኛሉ። እንደዛም ሆኖ፣ ከፍተኛ ለሆነ ሁከት፣ በተለይም ጾታን መሠረት ላደረጉና በኢንተርኔትም ሆነ ከኢንተርኔት ውጪ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጋላጭ ናቸው” ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ መናገራቸውን ርዕሰ-አንቀጹ ይጠቅሳል።

እንደዛም ሆኖ፣ “ግጭትን ለመከላከል፣ ሰላምን ለመገንባት እና ጸጥታን ለማስፈን፣ እንዲሁም የሽብር ጥቃትን ለመመከት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ሴቶች እና ልጃገረዶች በውሳኔ ሰጭነት ሚና ውስጥ በበቂ አለተወከሉም” ሲሉ አክለዋል አምባሳደር ግሪንፊልድ።

“አደገኛ አክራሪዎች ትንኮሳን፣ ሁከትን እና ሰቆቃን ሆን በለው በኢንተርኔት በሰፊው በመፈጸም ላይ ናቸው። ይህም በዚህ አያበቃም፣ ወደ አካላዊ ጥቃት በመሻገር ሴቶችን መኖሪያ ስፍራቸው እና የሚገኙበት ማኅበረሰብ ድረስ በመዝለቅ ይቀጥላል። ዓላማውም

መሪዎችን ዝም ለማሰኘት እና ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማፈን ነው” ብለዋል አምባሳደር ግሪንፊልድ።

በመሆኑም፣ የሽብር ጥቃቶችን ለመቀልበስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ፣ የሴቶች እና የወንዶች የተለያዩ ፍላጎቶች ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው፣ ሲል ርዕሰ-አንቀጹ በመቀጠል፣ ይህም ማለት ሴቶችን በጸረ-ሽብር እንቅስቃሴ ጥረቶች ውስጥ ተሳታፊ ማድረግ ነው ብሏል።

“ሽብርን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ውስጥ ሴቶችን አለማሳተፍ፣ አደገኛ አክራሪነትን በማስወገድ ረገድ ሊኖራቸው የሚችለውን ድርሻ ማባከን ነው።” ያሉት አምባሳደር ግሪንፊልድ። “አደገኛ አክራሪዎች ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን፣ አባሎችን ለመመልመልና ማኅበረሰቦችን ለማሸበር እንደ መሳሪያ በመጠቀም ላይ ባሉበት ወቅት፣ የጾታ ጉዳይ የጸረ ሽብር ጥረቶች ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖ ወይም በተቃራኒው ሊደርስበት የሚችለውን ተጽእኖ ማጤን አስፈላጊ ነው” ሲሉም አክለዋል።

በሁሉም እርከኖች ሽብርን ለመከላከል በሚሰጡ ምላሾች፣ ሴቶች የራሳቸውን እይታ እና ልምድ የሚያክሉ ከሆነ፣ የጸረ ሽብር ዘመቻው ውጤታማ እና ዘላቂነት ያለው ይሆናል።

“ሰብዓዊ መብትን መጠበቅ፤ ሽብርተኝነትን እና አደገኛ አክራሪነትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን፣ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን በእኩል፣ በሙሉ እና ትርጉም ባለው መንገድ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከማድረጉ በተጨማሪ ለውጤታማነቱም አስቻይ ሆኔታዎችን ይፈጥራል። የሽብር ጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ልጃገረዶችን ፍላጎት ማሟላት፣ ጾታን ከግምት ያስገባ የአሠራር ዘይቤን ማሳደግ፣ እና በጸጥታ ጉዳይ በሚሰሩ ስራዎች ውስጥ የሴቶችን ተሳታፊነት ማሳደግ፣ እንዲሁም ፍትህን፣ ሰብዓዊ መብትን እና የሕግ የበላይነትን ማበረታታት ወሳኝ ነው” ብለዋል አምባሳዳር ግሪንፊልድ።

“ሰብዓዊ መብትን ባከበረ እና የጾታ እኩልነት በሁሉም መስክ መካተት ያለብበት ጉዳይ መሆኑን በሚያረጋግጥ መንገድ፤ ሽብርተኝነትን እና አደገኛ አክራሪነትን ለመቀልበስ እንዲሁም ጾታን መሠረት ያደረግ ጥቃትን ለመከላከል፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከሲቪል ማኅበረሰብ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ዓባል ሀገራት ጋር መሥራቷን ትቀጥላለች”

ሲሉ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ መናገራቸውን ጠቅሶ ርዕሰ አንቀጹ ሃተታውን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG