ህወሓት በአማራ ክልል ለፈጸማቸው የግፍ አድራጎቶች (አረመኒያዊ ድርጊት) ተጠያቂ መሆን አለበት

“በቅርቡ አምነስቲ ኢንተርናሺናል ባወጣው ሪፖርቱ እንደዘረዘረው የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር ተባባሪ (ግንኙነት ያላቸው?) ተዋጊዎች በኢትዮጵያ በአማራ ክልል ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የጭካኔ አድራጎቶች መፈጸማቸውን የሚገልጹት ሪፖርቶች ዩናይትድ ስቴትስን በከባዱ አሳስበዋል” ሲል የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ ሃተታውን ይጀምራል።

የትግራይ ኃይሎች ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ጭና እና ቆቦ ከተሞችን መቆጣጣራቸውን ተከትሎ በነሃሴ ወር መጨረሻ እና መስከረም መጀመሪያ ላይ ጥቃቱ እንደጀመረ ርዕሰ አንቀጹ አውስቷል።

"የአስገድዶ መድፈር ተግባር በሰፊው ተፈጽሟል። ሰዎች በዘፈቀደ ተገድለዋል። ከሆስፒታሎች ጭምር ንብረት ተዘርፏል” ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ የአፍሪካ ቀንድ እና የታላላቅ ኃይቆች ክልል ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን መናገራቸዋን የጠቀሰው የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ “በሰሜን ምስራቅ አማራ በምትገኘው የቆቦ ከተማ የትግራይ ተዋጊዎች ሆን ብለው ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን አመልክቷል።

ከሐምሌ ወር አንስቶም ከሌላዋ የክልሉ ከተማ ጭና ውስጥ እና በዙሪያዋም የትግራይ ኃይሎች ብዛት ያላቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች ደፍረዋል ያለው ርዕሰ አንቀጽ አምነስቲ ኢንተርናሺናል በሪፖርቱ እንደገለጸው ጾታዊ ጥቃት አድራሶቹ በሰለባዎቻቸው ላይ ድብደባ የመግደል ዛቻ እና በዘውግ (በብሄር) ማንነት ላይ የተነጣጠሩ አዋራጅ ስድቦችን መሳደብን ጨምሮ ሰቅጣጭ ግፍ እንዳደረሱባቸው አመልክቷል።

ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ብዙዎቹ ከባድ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል አክሏል።

“አምነስቲ ኢንተርናሺናል ካሁን ቀደም ባደረገው ክትትልም የትግራይ ተዋጊዎች ነፋስ መውጫ ከተማ ውስጥ በአማራ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸውን ዘግቧል” ካለ በኋላ ርዕሰ አንቀጹ አክሎም አምነስቲ በሌሎችም የአማራ ክልል አካባቢዎች የአስገድዶ መድፈር አድራጎት መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ አስተማማኝ ሪፖርቶች የደረሱት መሆኑን አስታውሷል።

የትግራይ ተዋጊዎች በሁለቱም አካባቢዎች ... በቆቦ እና በጭና .. ከመኖሪያ ቤቶቻቸው እና ከመደብሮቻቸው ንብረት መዝረፋቸውን፣ ክሊኒኮች እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ላይ ዝርፊያ እና ውድመት ማድረሳቸውን ነዋሪዎች ለአምነስቲ ኢንተርናሺናል መናገራቸውን ርዕሰ አንቀጹ ገልፆ በህክምና ተቁዋማት ላይ የደረሰው ዝርፊያ እና ውድመት የህክምና እርዳታ የሚሹ አስገድዶ የመድፈር ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴቶች እና ሌሎችም ነዋሪዎች በአካባቢያቸው በህክምና እንዳይረዱ አድርጓል ብሏል።

የጭካኔ ድርጊቶች ሪፖርቶች መቀጠላቸው የጦርነቱን ባስቸኩዋይ መቆም አስፈላጊነት ያሰምርበታል ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ማሳሰባቸውን የጠቀሰው ርዕሰ አንቀፁ ቃል አቀባዩ አያይዘውም “ውጊያው እንዲቆም፣ የጭካኔ አድራጎቶች እንዲገቱ፥ ህይወት አድን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚስፈልጋቸው ሳይደናቀፍ እንዲደርስ፤ ብሎም ግጭቱ ሰላማዊ ማብቂያ እንዲያገኝ በግጭቱ ያሉትን ወገኖች መወትወታችንን እንቀጥላለን” ያሉትን አውስቷል።

“የታጠቁ ኃይሎች በሙሉ በሲቪሎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መፈጸምን እንዲያወግዙ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲያበቁ እናሳስባለን። ለቀውሱ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ይቻል ዘንድም የተፈጸሙትን የጭካኔ ድርጊቶች ላይ ተአማኒነት ያለው ምርመራ እንዲካሄድ፤ ፈጻሚዎቹ በተጠያቂነት መያዝ እንዳለባቸው አሁንም ጽኑ አቁዋማችን ነው” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የተናገሩትን ጠቅሶ የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ ሃተታውን ደምድሟል።