በኢትዮጵያ ያገረሸው ግጭት

በኢትዮጵያ ያገረሸው ግጭት

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሰብዓዊ ተግባሮችን ለማከናወን እንዲቻል ባለፈው መጋቢት ውጊያ ማቆማቸው ሁከቱ ለአምስት ወራት ጋብ እንዲልና ችግር ወደ ጠናባቸው ክልሎች ህይወት አድን ዕርዳታ እንዲደርስ ለማድረግ ማስቻሉን ርዕሰ አንቀፁ በመግቢያው ላይ አስፍሯል።

የውጊያው መቆም አስከፊውን ግጭት እስከወዲያኛው ወደማቆም ይወስዳል የሚል ተስፋን አጭሮ እንደነበር የጠቆመው ይህ ርዕሰ አንቀፅ ጥሉ በትግራይና በአማራ ክልሎች ድንበር ላይ ነኀሴ 17 እንደገና ሲጀምር ግን ያ ተስፋ መጨለሙንና ጦርነቱ እንደገና ለመጀመሩ አንዱ ሌላኛውን እንደሚከስ ይጠቁማል።

በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል ያለው ግጭት ከጀመረ ወደ ሁለት ዓመት ገደማ እንደሆነው በማስታወስ ይቀጥልና በጌንት ዩኒቨርሲቲ ግምት ለሦስት ዓመታት በከፋ ድርቅ በተመታችውና በቂ ሰብል ባልሰበሰበችው ሃገር ውስጥ ከሃምሣ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ሰው በጦርነቱ ውስጥ መሞቱን፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደሚለው ደግሞ ትግራይ ውስጥ ከሚገኙት 5 ሚሊዮን ተኩል ሰው ውስጥ ግማሹ እጅግ የበረታ የምግብ እጥረት ላይ መሆኑን ያትታል።

ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ ዕርዳታ ከሚለግሱት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ የበዛውን ግዙፍ ድጋፍ የምትሰጥ ሃገር መሆኗንና ይህም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን “ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልሎችና ሕዝብ ለማዳረስ ቁርጠኞች ነን” ያሉትን

እንደሚያንፀባርቅ ርዕሰ አንቀፁ ጠቁሞ፣ ብሊንከን አክለውም ዩናይትድ ስቴትስ በመላ ሃገሪቱ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ ለልማትና ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል 1.2 ቢሊዮን ዶላር መለገሷን መጠቆማቸውን፤ ይህም “ድርቅን ለመቋቋም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለሰላም ግንባታ፣ ለጤና፣ ለትምህርትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ለሥልጠና የሚውል ነው” ማለታቸውን አመልክቷል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን የጦርነቱን ማገርሸት በመግለጫቸው ማውገዛቸውን ርዕሰ አንቀፁ አስታውቋል። “በቅርቡ በጦር ግንባር የተፈፀመው ትንኮሳ፣ የቀረርቶና የፉከራ ንግግሮችና የተኩሱ በዘላቂነት አለመቆም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ደኅንነትና ብልፅግናን ወደማስገኘት ሊወስድ የሚችለውን ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት መጀመርን ያዘገያል፤ ወደ ጦርነት መመለስ ስቃይንና መከራን፣ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣንና የምጣኔ ኃብት ድቀትን ማብዛትና ማስፋፋትን ያስከትላል” ማለታቸውን ገልጿል።

ምኒስትር ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግሥት ተዳራዳሪ ቡድን ማቋቋሙንና ለንግግር ፍቃደኝነቱን መግለፁን አድንቀው “ሁሉም ወገኖች በረድዔት አቅራቢዎች የሚካሄደውን ምግብና ነዳጅ የማዳረስን ጥረት እንዲያከብሩ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታን ለወታደራዊ ጉዳይ ከማዋል እንዲቆጠቡ፣ እንዲሁም መሠረታዊ አገልግሎቶች ለሚያስፈልጓቸው ሁሉ መልሰው እንዲቀጥሉ እንዲያደርጉ” እንደሚጠይቁም ተናግሯል።

“ተኩስ ያለቅድመ-ሁኔታ በዘላቂነት እንዲቆምና በውጤቱም ግጭቱ እንዲያበቃ ለማስቻል የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ጥረቶቻቸውን

እንዲያጠናክሩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ጥሪ አድርገዋል” ሲል ርዕሰ አንቀፁ መልዕክቱን ደምድሟል።