የሽብርተኞችን የገንዘብ ምንጭ ማድረቅ

"አይሲስን ድል ለመምታት የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ጥምረት" በተባለው ኅብረት ስር የሚሠራው "የአይሲስ ፋይናንስ አስወጋጅ" በእንግሊዝኛ የአህጽሮት መጠሪያው ሲ አይ ኤፍ ጂ 17ኛውን ስብሰባውን አካሂዷል።

ባለፈው ኅዳር በተካሄደው ስብሰባው አይሲስን ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ ድል ማደረግ አሁንም ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ማረጋገጡን በማውሳት የዛሬው ርዕሰ አንቀጽ ሀተታውን ይጀምራል። ሲ አይ ኤፍ ጂ በግንቦት ወር የኋለኛውን ስብሰባውን ማካሄዱን ተከትሎ ዐለም አቀፉ ጸረ አይሲስ ጥምረት በመካከለኛ ምስራቅ ሀገሮች የቡድኑን ዋና ዋና የፋይናንስ መሪዎች እና ኅላፊዎችን ዒላማው አድርጎ ተንቀሳቅሷል።

ከዚህም በተጨማሪ የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይል በሶሪያ እና በኢራቅ አይሲስ የሚያካሄደውን አመጽ ለመዋጋት ኮሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች እና ከኢራቅ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ርዕሰ አንቀጹ አውስቷል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች አይሲስ በዐለም ዙሪያ ጥቃት ለማድረስ የማቀድ፥ ገንዘቡን የመሰብሰብ እና ዕቅዱን ዳር የማድረስ አቅሙን አዳክሞበታል ሲል ርዕሰ አንቀጹ ያወሳል።

ርዕሰ አንቀጹ ጽሁፉን በመቀጠል አይሲስ በዚህ እ አ አ በ 2022 ዐመተ ምህረት ቢያጣም ዋናው የቡድኑ አስኳል "አይሲስ ኮር "አሁንም እንዳለ ነው ካለ በኋላ ቡድኑ ሶሪያ እና ኢራቅ ውስጥ የ25 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ገንዘብ እንዳለው አትቷል።

ቡድኑ ይህን ያህል ገንዘብ ሊያከማች የቻለው እ አ አ ከ 2014 እስከ 2017 ዓ.ም ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ ግዛቶች በተቆጣጠረ ጊዜ ነዳጅ ዘይት በመሸጥ፥ ከመንግሥት ካዝና በመበዝበዝ፥ ባንኮችን በማስዘረፍ መሆኑን ርዕሰ አንቀጹ አውስቷል።

የዓለም አቀፉ ጸረ አይሲስ ጥምረት ወታደራዊ ኃይሎች እና የአካባቢው ሀገሮች ሕግ አስከባሪ ኃይሎች በትብብር በሚወስዷቸው ዕርምጃዎች የአይሲስ ገቢ እየቀጠነ መጥቷል። በመሆኑም መሪዎቹ ነጋዲዎችን እያስፈራሩ ገንዘብ ይነጥቃሉ። ሰው እያገቱ ማስለቀቂያ ያስከፍላሉ፥ ይዘርፋሉ። አልፎ አልፎም ከውጭ የገንዘብ ስጦታ ያገኛሉ።

የአይሲስን የገንዘብ ምንጭ ለማድረቅ የሚንቀሳቀሰው አካል ባለፈው ዐመት ውስጥ ትኩረቱን የቡድኑ ቅርንጫፎች፥ መረቦች እና ህዋሶች ህዝብ እያሸበሩ ግዛቶችን ለመቆጣጠር ወደሚንቀሳቀሱባቸው የአፍሪካ አካባቢዎች ማዞሩን ርዕሰ አንቀጹ አመልክቷል። ከቀንደኞቹ የአይሲስ ቅርንጫፎች አንዱ የሶማሊያው አይሲስ መሆኑን ሲ አይ ኤፍ ጂ ገልጿል። አይሲስ ሶማሊያ አብዛኛውን ገቢውን የሚሰበስበው የሀገሪቱን ነገዴዎች እና ነዋሪዎችን እያስፈራራ ገንዘብ በመቀበል ሲሆን በዚህ መንገድ በየወሩ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ይሰበስባል።

የአይሲስን የገንዘብ ምንጭ ለማድረቅ የሚንቀሳቀሰው አካል ሲ አይ ኤፍ ጂ ዩናይትድ ስቴትስ በሶማሊያው አይሲስ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ላይ እ አ አ ባለፈው ህዳር አንድ ቀን በጣለችው ማዕቀብ መደሰቱን ገልጾ ሌሎችም ሀገሮች ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።

ሲ አይ ኤፍ ጂ የአይሲስን የፋይናንስ መረብ ለመበጣጠስ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ፥ ታንዜኒያ፥ ዩጋንዳ፥ ሞዛምቢክ እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች እየሰራ መሆኑን ርዕሰ አንቀጹ ገልጿል። አይሲስን ድል ለመምታት የተዋቀረው ዐለም አቀፍ ጥምረት የቡድኑን የገንዘብ ድጋፍ መረብ ይበጣጥሳል። ቡድኑን ከነቅርንጫፎቹ ድል ይመታል በማለት ርዕሰ አንቀጹ ጽሁፉን ደምድሟል።