የኮሎምበሰ ቀን 2020 የኮሎምቦስ ልውውጥ

ፎቶ ፋይል፦ የኮሎምበሰ ቀን በኒው ዮርክ

ፎቶ ፋይል፦ የኮሎምበሰ ቀን በኒው ዮርክ

“እኤአ፣ ኦክተበር 12/1492 ዓመተ ምህረት፣ በክርስቶፈር ኮሎምበስ የተመሩ ሶስት የስፔን መርከቦች፣ ዛሬ ባህማስ ከምትባለው ደሴት ላይ አረፉ” ይላል፣ የእለቱ ርእሰ አንቀጽ ሀታተውን ሲጀምር፡፡ ርዕሰ አንቀጹ በመቀጠልም፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በየዓመቱ የሚታሰበው፣ የኮሎምበስ ቀን፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ የምግብ ልውውጥ፣ እንስሳት፣ ተክሎች፣ ህዝቦችና ዓለምን የለወጡ በሽታዎች ሳይቀሩ፣ የኮሎምቦስ ልውውጦች ተብለው ይታወቃሉ ብሏል ፡፡ አያይዞም፣ በዚያ የተነሳ በብዙ የታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ፣ እኤአ 1492 ዓመተ ምህረት፣ በጣም ወሳኝ ዓመት ተደርጎ ይታሰባል ብሏል ፡፡

“የዓለም ህዝብ ብዛት፣ ከ1492 ጀምሮ በአራት ጊዜ እጥፍ ጨምሯል” ያለው ርዕሰ አንቀጽ፣ በተለይ እኤአ በ1650 እና 1850 መካከል፣ በእጥፍ መጨመሩን ያስረዳል፡፡ “ምንም እንኳ ለዚህ ትልቅ እድገት፣ አስተዋጽኦ ያደረጉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ትልቁና ዋነኛው፣ የምግብ አቅርቦት ስርጭት፣ እየተሻሻለና እየጨመረ መምጣቱ፣ ዋነኛው መሆኑን፣” ርዕሰ አንቀጹ አስረድቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፣ በተለይ “ኔቲቭ አሜሪካንስ” የሚባሉት የሃገሬው ተወላጅ አሜሪካውያን ምግቦች የሆኑት፣ እንደ በቆሎ፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ኦቾሎኒ (ለውዝ) ፣ አናናስ፣ ማኒዮክ፣ በርበሬ፣ እና የኮካዋ ባቄላ የመሳሰሉት ዋነኞቹ መሆናቸውን ርእሰ አንቀጹ ዘርዝሯል፡፡

“ድንች፣ በመካከለኛውና ሰሜን አውሮፓ፣ እጅግ ተወዳጅና አስፈላጊ ምግብ እየሆነ መጥቷል” ያለው ርእሰ አንቀጽ፣ “በቆሎና ማኖይክ ወይም ካሳቫ የሚባሉት ተክሎች ደግሞ፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን፣ በአፍሪካ እንዲተዋወቁ መደረጋቸውንና ከአገሬው የባህል ሰብሎች ውስጥ፣ ዋነኛው መሆናቸውን ርእሰ አንቀጹ ጽፏል፡

ለቻይና የተዋወቁት የአዲስ ዓለም፣ አዲስ የምግብ ሰብሎችም፣ በተለይም፣ እንደ ድንች፣ በቆሎ እና ኦቾሎኒ የመሳሰሉት፣ እኤአ ከ1500 እስከ 1650 ድረስ እየጨመረ ለመጣው የቻይና ህዝብ እድገት፣ ምክንያት መሆናቸውን፣ ርዕሰ አንቀጹ አስረድቷል፡፡

ርእሰ አንቀጹ በመቀጠል፣ የኮሎምቦስ ልውውጥ፣ አዳዲስ ምግቦችን፣ በየትኛውም የዓለም ጫፉ ላሉ ህዝቦች ያስተዋወቀ ነው ብሏል፡፡ እኤአ ከ1492 በፊት፣ በፍሎሪዳ ብርቱካን እሚባል አልነበረም፣ በኢኳዶር ሙዝ አይታወቅም፣ በሃንጋሪ ፓፕሪካ አልታወቀም፡፡ ልውውጡ ቲማቲምን ወደ ጣልያን፣ ቡናን ወደ ኢንዶኔዥያና ኮሎምቢያ፣ የጎማ ዛፎችን ወደ አፍሪካ፣ የሚያቃጥሉ በርበሬዎችን ወደ ታይላንድ እና ቻይና፣ እንዲሁም ቼኮለትን ወደ ስዊዘርላንድ እየወሰደ፣ ማስተዋወቁን ርእሰ አንቀጹ ዘርዝሯል፡፡

“በባሃማስ ደሴት ላይ ፣ መሃለቃቸውን የጣሉ ሶስት መርከቦች፣ በዓለም ታሪክ፣ ጨርሶ ያልታሰበ ለውጥ አምጥተዋል፣” ያለው ርዕሰ አንቀጽ፣ ይህም፣ “የሰዎችን የወደፊት እጣ ፈንታ፣ ለክፍለ ዘመናት ቀይሯል” ብሏል፡፡ ይህ መሆኑም አዲስ ክፍለ ዓለም ወይም አህጉር መኖሩን ማሳወቁ ብቻ ሳይሆን፣ በምድረ ገጽ ላይ ቋሚ ግንኙነት እንዲኖር፣ ንግድ እንዲስፋፋ፣ የሀሳብ ልውውጥ እንዲበዛ፣ የባህል ግንኙነቶችና ልውውጦች እንዲኖሩ፣ ሁኔታዎችን አመቻችቷል” ብሏል ርእሰ አንቀጹ፡፡

በመጨረሻም እኤአ “1492፣ የዓለም ህዝቦችን፣ እንደ አንድ ማኅበረሰብ፣ በአንድነት እንዲመጡ አድርጓቸዋል” በማለት ርእሰ አንቀጹ ጽሁፉን ደምድሟል፡፡