Accessibility links

Breaking News

ረሃብን ማሸነፍ


ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረትን ለማሸነፍ ሦስት መንገዶች አስፈላጊ መሆናቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የዐለም አቀፍ ልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ማስገንዘባቸውን በመግለፅ የዛሬው ርዕሰ አንቀጽ ሐተታውን ጀምሯል።

ሳማንታ ፓወር ይህን የተናገሩት የዘንድሮ እ አ አ 2021 ዐመተ ምህረት የምግብ ሥርዐት የመሪዎች ጉባዔ ከመከፈቱ እስቀድሞ በተካሄደው የሚንስትሮች ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር ነው።

ረሃብን ለማስወገድ ከሚያስፈልጉት መካከል አዳዲሶቹን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ ማዋል፥ መዋዕለ ነዋይን እጅግ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ማፍሰስ፥ በመንግሥት በሚመደብ ገንዘብ አማካይነት የግሉን ዘርፍ ካፒታል እንዲያንቀሳቅስ ማበረታታትን ይጨምራል።

ግጭቶች በየቦታው መቀስቀሳቸው፥ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎች እና አሁንም አብዝቶ መዛመቱን የቀጠለው የኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሽኝ አንድ ላይ ሆነው ያስከተሉት እጅግ የከበደ አደጋ በቅርብ ጊዚያት ያስመዘገብናቸውን ድሎች አብዛኞቹ አበላሽቶብናል ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የዐለም አቀፍ ልማት ተራድዖ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ማስጠንቀቃቸውን ርዕሰ አንቀጹ አውስቷል።

ባሁኑ ወቅት ሥር በሰደደ ሁኔታ ለተራዘመ ጊዜ ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ለህይወታቸው በሚያሰጋ ደረጃ ለአጣዳፊ ረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በአለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ በሃያ ከመቶ ጨምሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረሃብን ሙሉ በሙሉ ከዐለም ላይ ለማስወገድ ያወጣውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የቀረን ከአስር ዐመት ያነሰ ጊዜ በሆነበት ባሁኑ ወቅት ይህ አሃዝ እጅግ የሚያሳስብ መሆኑንም ርዕሰ አንቀጹ አመልክቷል።

የዩኤስአይዲ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ህዝብን ለረሃብ የሚዳርገው ግንባር ቀደም ምክንያት አሁንም ግጭት እና ጦርነት ነው ብለዋል።

"መንግሥታት የገዛ ህዝባቸውን የሚያስርቡ እና ምግብን በጦርነት መሳሪያነት የሚጠቀሙ ከሆነ ረሃብን ልናስወግድ አንችልም። ይህ የሚደረገው ቤተሰቦችን ሆን ብሎ ከቀዬ በማፈናቀል፥ ሰብልን እና የቀንድ ከብቶችን በማውደም፥ የሰብዐዊ ርዳታ አቅርቦት ለተረጂዎች እንዳይደርስ በማደናቀፍ ፥ ሰብዐዊ ረድኤት ለማቅረብ የተሰማሩ የርዳታ ሰራተኞች ላይ ጥቃት በማድረስ ነው።

ህዝብን ሆን ብሎ ለረሃብ የመዳረግ አድራጎትን ሳናወላውል ድምጻችንን ከፍ አድርገን ማውገዝ እና ችግር ላይ ላሉ ሰዎች ሰብዐዊ ርዳታ እንዲደርስ መታገል አለብን።" ብለዋል።

ሆኖም ብዙውን ጊዜ በዐለም ዙሪያ ሲደረግ እንደቆየው ትኩረታችንን ሰብዓዊ ረድዔት ና የምግብ ድጋፍ መስጠት ላይ ብቻ አድርገን የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ ጥረታችን ቅድሚያ መስጠት አይኖርብንም ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ር ዕሰ አንቀጹ ጠቅሷል።

"ለባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለማሳደግ የሚጠቅሙዋቸውን መሳሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች ልንሰጣቸው ይገባል። የፓሪሱን የአየር ንብረት ለማሳካት እየተጣደፍን በምንገኝበት ባሁኑ ወቅት እየተባባሱ ያሉትን ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ የሆኑ አደጋዎች ለመቋቋም የሚረዱዋቸውንም እንዲሁ።" ሲሉ ሳማንታ ፓወር አስገንዝበዋል።

የዛሬው ርዕሰ አንቀጽ በመቀጠል የባይደን-ሃሪስ አስተዳደር የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ ፤ የምግብ ዕጥረትን ለማስወገድ እና ህዝብ የሚከሰቱ አደጋዎችን ጠንክረው የመቋቋም አቅማቸው እንዲዳብር "ፊድ ዘ ፊውቸር" የተባለውን ረሃብን ለማስወገድ የተወጠነ መርሃ ግብር ምሰሶው አድርጎ አስተዋፅኦ ማደርጉን ይቀጥላል ብሏል።

የተመጣጠነ ምግብ ዕጦትን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ለማስወገድ በዐለም ዙሪያ ከአጋሮቻችን ጋር አብረን ለመስራት ዝግጁዎች ነን ሲሉ የዩ ኤስ አይ ዲ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር የተናገሩትን ጠቅሶ ርዕሰ አንቀፁ ሐተታውን አጠቃሏል።

XS
SM
MD
LG