በአውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ጥር ወር ውስጥ በሚመጣው ሦስተኛው ሰኞ ላይ አሜሪካውያን የሬቨርንድ ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግን መታሰቢያ እለት አክብረው ይውላሉ፡፡
ዶ/ር ኪንግ የደቡብ አላባማ ክፍለ ግዛት የባፕቲስት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ሲሆኑ በዩናይትድ ስቴትስ የዘር መድልዎን በመቃወም ለእኩልነት የሚደረገው ትግል መሪ ነበሩ፡፡ ጥር 7/2015፣ 94ኛው የልደት በዓላቸው የሚያከብሩበት እለት ነበር፡፡
እኤአ 1865 የዩናይትድ ስቴትስ የእርስ በርስ ጦርነት ያበቃበት እና ባርነትን በህግ የከለከለው 13ኛው የህገመንግሥቱ ማሻሻያ የወጣበት ወቅት ነው፡፡ እንዲሁም የዘር ማህበረሰብ አባላትና ሴቶችን ጨምሮ በብዙዎቹ አሜሪካውያን ዘንድ የጂም ክሮ ህጎች ተብለው የሚታወቁትን በመቃወም እንዲሁም እኤአ በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ፖለቲካዊ ውክልና ለሌላቸውና በቁጥር አነስተኛ ለሆኑት የሰቪል መብቶች ጥበቃ እንዲደረግ በመጠየቅ በሺዎቹ የሚቆጠሩ አሜሪካውያን አደባባይ የወጡበትና ሁከትም የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡
እነዚህ የመንግሥትና የአካባቢው ህጎች የዘር መለያየት እና ያፈጠጠን ግልጽ መድሎዎን ህጋዊ በማድረግ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በማህበረሰቡ የሲቪል ጠባቂ ቡድኖች በኃይል የሚተገበሩ ነበሩ፡፡
ይህን ስርዓት ለመለወጥ የሞከሩ አፍሪካ አሜሪካዊያን ተመጠጣጣኝ ያልሆነ የአፓርታይድ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን ብዙዎቹንም የመብት ተሟጋቾች ለሞት ዳርጓል፡፡
በዚህ አውድ ውስጥ ዶ/ር ኪንግ የማህተማ ጋንዲን የሰላማዊ ተቃውሞ መርሆዎች በመከተል የተከታዮቻቸውን መጠነ ሰፊ አድማ፣ የመቀመጥ እና ሰላማዊ የሰልፍ ጉዞዎችና የህዝባዊ እምቢተኝነትን መርተዋል፡፡ በተቃዋሚዎቹ ላይ በተደጋጋሚ የሚወሰዱ መጠን ያለፉ የበቀል እምርጃዎች በተቀረው የአገሪቱ ክፍል አስቸኳይ ለውጥ የሚያስፈልግ መሆኑን አሳይተዋል፡፡
ዶ/ር ኪንግ የድካማቸውን ፍሬ ለማጣጣም እድሉ አልነበራቸውም፡፡ እኤአ ሚያዝያ 4/1968፣ በ39 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡ ይሁን እንጂ በአስርት ዓመታት የዘር ልዩነት ህጎች ተሰርዘዋል፡፡ ዛሬ መድልዎ የተወገዘና በሕግም የሚያስቀጣ ወንጀል ሆኗል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን “ዛሬ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ሰዎች ያንን የሰልፍ ጉዞ ቀጥለዋል፡፡ ሥልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙትን ለመጋፈጥ፣ ጥላቻና መድልዎን ለመቃወም፣ የመምረጥ መብት እንዲጠበቅ፣ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ እንዲኖር፣ የጤና እንክብካቤ፣ የመኖሪያ ቤትና ትምህርት እንዲኖር ድምጻምቸውን ከፍ አድርገዋል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ባይደን አክለውም “በዚህች እለት ለአገራችንና ዓለማችን ስለ ህሊናችን ጥሪ ያቀረብልንን ሰው ትሩፋት እናስባለን፡፡” ብለዋል፡፡