Accessibility links

Breaking News

ዩናይትድ ስቴትስ የኤርትራን መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ጦር አዛዥ ጄኔራልን ተጠያቂ አደረገች


“ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት የኤርትራ መከላከያ ኃይል ከፈጸማቸው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ጦር አዛዥ ጄኔራል ፊሊፖስ ወልደዮሃንስን በተለይ ተጠያቂ አድርጋለች” ሲል ይንደረደራል የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ የቅርብ ጊዜውን የዩናይትድ ስቴትስ ውሳኔ አስመልክቶ ባወጣው እና የመንግስቱን አቋም በሚያንጸባርቀው ጽሁፍ።

ርዕሰ አንቀጹ በመቀጠልም “ጀነራል ፊሊፖስ ተጠያቂ የተደረጉበት ይህ ውሳኔ ዓለም አቀፉ የማግኒትስኪ የሰብአዊ መብቶች ተጠያቂነት ሕግ በመባል የሚታወቀውን የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በዓለም ዙሪያ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እና ሙስና ፈፃሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የጸደቀ ድንጋጌ ተግባራዊ በሚያደርገው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ቁጥር 13818 መሠረት የተወሰደ ነው” ሲል ያብራራል።

“በፊሊጶስ አመራር ስር ያሉ የኤርትራ ወታደሮች” ርዕሰ አንቀጹ አጽንኦት በመስጠት ይቀጥላል። “በፊሊጶስ አመራር ስር ያሉ የኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቪሎችን ገድለዋል፣ አስገድደው ደፍረዋል፣ አሰቃይተዋል፣ ንብረት አውድመዋል፤ እንዲሁም የንግድ ድርጅቶችን ዘርፈዋል።”

ተፈናቃዮች እንደተናገሩትም “የኤርትራ መከላከያ ኃይል በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጉዳት ለማድረስ በተቀነባበረ ዘዴ ጥረት አድርጓል።” ሲል ይከሳል።

የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችም ሲያስረዱ “ሲቪሎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ለማድረግ የታቀደ፡ ‘ጠላት ሊጠቀምበት ይችላል’ የተባለ ነገር በሙሉ እንዲወድም የሚደረግበትን ወታደራዊ ፖሊሲም ተግባራዊ አድርጓል” ሲል ርዕሰ አንቀጹ ይዘረዝራል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አጥብቃ ታወግዛለች።”ያለው የዩናይትድ ስቴትስን መንግስት አቋም የሚያንጸባርቀው ርዕሰ አንቀጽ አክሎም “ይህም ግድያን፣ ነዋሪዎችን ከቀያቸው በኃይል ማፈናቀልን እና የተቀነባበሩ ወሲባዊ ጥቃቶችን ይጨምራል። በመሆኑም እነኚህን የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ የፈጸሙ ወገኖች ግልፅ በሆነ የህግ ሂደት ተጠያቂ መሆን አለባቸው።” ብሏል።

“የኤርትራ መከላከያ ኃይል ባለፈው የሰኔ ወር አገሪቱን ለቆ ከወጣ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦሩ ኃይሉ አባላት ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ዩናይትድ ስቴትስን አሳስቧታል።” ያለው የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ አያይዞም “የኤርትራ መንግሥት ወታደራዊ ኃይሉን በአስቸኳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ እንዲያወጣ ጥሪያችንን እናሰማለን” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ ያቀረቡትን ሃሳብ አንጸባርቋል።

በተጨማሪም “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርን ጨምሮ በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን በደል እንዲያቆሙ፣ ግጭቱን ለማርገብ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ ተደራሽነት እንዲኖር እና በድርድር ለሚደረስ የተኩስ አቁም ቃል እንዲገቡ ዩናይትድ ስቴትስ ማሳሰቧን ትቀጥላለች” ያሉበትንም አክሏል።

ርዕሰ አንቀጹ በመቀጠልም፡ “ይህ በኤርትራ መንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች አዛዥ ላይ የተወሰደው እርምጃ የዩናይትድ ስቴትስ የእነኝህን አስነዋሪ ድርጊቶች ፈጻሚዎች ዋጋ ለማስከፈል ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል” ያሉት በዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት የውጭ ሃገር መንግስታት፤ ቡድኖች እና ግለሰቦችን ንብረት ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ድሬክተር አንድሪያ ጋኪ “ኤርትራ ኃይሏን በአስቸኳይ፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ፤ በግጭቱ ያሉ ወገኖች የተኩስ አቁም ድርድር እንዲጀምሩ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያቆሙ እናሳስባለን።” ያሉትን ጠቅሷል።

“በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ሰላማዊ እልባት ያገኝ ዘንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተባብረው ግፊት ማድረግ አለባቸው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የተናገሩትን ጠቅሶ የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ ሃተታውን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG