Accessibility links

Breaking News

ነጻ ፕሬስን ማክበር


በነጻ ፕሬስ መንግሥታት ተጠያቂ ይሆናሉ፥ ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም እና ሙሰኝነትንም ያጋልጣል፤ ህዝብ በሚገባ መረጃ ማግኘቱን ለማረጋገጥም ነጻ ፕሬስ ይጠቅማል። በብዙ ሀገሮች ጋዜጠኞች በሚያጠናቅሯቸው ዘገባዎች ምክንያት ጥቃት ይደርስባቸዋል ወይም ለእስር ይዳረጋሉ በማለት "ነጻ ፕሬስን ማክበር" በሚል ርዕስ የወጣው ርዕሰ አንቀጽ ጽሁፉን ይጀምራል።

የመናገር ነጻነትን መከበር ብለው ጋዜጠኞች የሚያከናውኑት ታላቅ ሥራ ዕውቅና ለመስጠት የዘንድሮ የኖቤል የሰላም ሽልማት ለሁለት ጋዜጠኞች መበርከቱን እነሱም የፊሊፒንሷ ማሪያ ሬዛ እና የሩስያው ዲሚትሪ ሙራቶቭ መሆናቸውን ርዕሰ አንቀጹ አውስቷል።

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ለኖቤል ተሸላሚዎቹ አክብሮታቸውን ለመግለፅ ባወጡት መግለጫ "ሬዛ እና ሙራቶቭ በዓለም ዙሪያ እንዳሉ አያሌ ጋዜጠኞች ሁሉ ሳይታክቱ እና ሳይፈሩ ሀቆችን ለማጣራት የሰሩ ጋዜጠኞች ናቸው፤ በስራቸው በስልጣን ያለአግባብ መጠቀምን እና ሙሰኝነትን እየተከታተሉ አጋልጠዋል፥ ግልጽነት እንዲኖር ጠይቀዋል" ሲሉ አውስተውላቸዋል። በጽናት ሰርተውም ነጻ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች አቋቁመዋል። ሊያፍኑዋቸው የተነሱ ኃይሎችንም ታግለዋል። ' ሲሉም ፕሬዚደንት ባይደን አስከትለው ተናግረዋል።

ርዕሰ አንቀፁ ጽሁፉን በመቀጠል ሬዛ እና ሙራቶቭ እንደሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸው ሁሉ ዕውነቱን ለመዘገብ ባላቸው ቁርጠኝነት ዋጋ እንዳስከፈላቸው አውስቷል። ያለማቋረጥ ወከባ ዛቻ በሀሰት ላይ የተመሰረተ ክስ ደርሶባቸዋል። ከዚያም ሲያልፍ ሙራቶቭ ባልደረቦቹ ህይወታቸውን አጥተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በስራቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ዛቻ፥ ወከባና ጥቃት እንደምታወግዝ ርዕሰ አንቀጹ አስገንዝቧል። በመንግሥታት የሚፈጸሙ እንዲህ ዐይነቶች አድራጎቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን ያመለከተው ርዕሰ አንቀጹ መንግሥታት ከአገር ውጭም ጭምር ጋዜጠኞች የሙስና ወይም የአፈና ድርጊቶቻቸውን ተከታትለው መዘገብ እንዳይችሉ ለማድረግ ጋዜጠኞች ያሉበትን ቦታ እና የመረጃ እና መልዕክት ልውውጦች ዲጂታል ስለላ አውታሮችን ያለአግባብ በመጠቀም ይከታተሏቸዋል ብሏል። ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት ሊዋከቡ ሊዛትባቸውም ሆነ አካላዊ ጥቃት ሊፈጸምባቸውም ሆነ ሊታሰሩ አይገባም ብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ "በዐለም ዙሪያ መገናኛ ብዙሃንን ለማፈን እየተባባሰ የሄደውን ጋዜጠኞች ላይ አካላዊ ጥቃት ማድረስን ማህበራዊ መገናኛ ላይ ማዋከብ እና ማስፈራራት እና መክሰስ የመሳሰለውን አድራጎት ልንቃወም ይገባል" ሲሉ የተናገሩትን ርዕሰ አንቀጹ ጠቅሷል።

ዩናይትድ ስቴትስ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ለመገናኛ ብዙሃን አባላትም ጨምር እንዲከበር የፕሬስ ነጻነት ላይ ጥቃት የሚሰነዘሩ ተጠያቂ እንዲሆን መሟገቷን እንደምትቀጥል አክሏል።

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን "ሬሳ ሙራቶቭ እና ሌሎችም በዓለም ዙሪያ ያሉ ጋዜጠኞች እነርሱ ለዕውነት ለራሱ የቆሙ በሚታገሉበት ዐለም አቀፍ ግንባር ላይ የተሰለፉ ናቸው፥ ሳይበገሩ በፋና ወጊነት ስላበረከቱት ስራቸው እናመሰግናቸዋለን" ሲሉ የተናገሩትን ጠቅሶ ርዐሰ አንቀጹ ጽሁፉን አጠቃልሏል።

XS
SM
MD
LG