Accessibility links

Breaking News

“ቸል የተባሉ” የትሮፒካል በሽታዎች መታሰቢያ ቀን


“ትሮፒካል” በሚል መጠሪያ በሚታወቀው የምድር ክፍል በሚገኙ አካባቢዎች በብዛት ለሚታዩትና “ቸል የተባሉ .. የተዘነጉ” የሚል መጠሪያ ለተሰጣቸው የበሽታ ዓይነቶች ትኩረት በመስጠት በአውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በያመቱ ጥር 30 የሚታሰብበት ዕለት መሆኑን ባለፈው ዕሁድ የዋለውን ዕለት በማስታወስ ይጀምራል የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ።

“እነኚህን የበሽታ ዓይነቶች ለመዋጋት የሚያስፈልገውን የመዋዕለ ለማሰባሰብ የሚያግዝ የፖለቲካ ፈቃደኝነት ለመሳብ ትኩረት የሚደረግበት ቀንም ነው፡፡” ብሏል።

ርዕሰ አንቀጹ አያይዞም “ይህ መጠሪያ የተሰጣቸው እነኚህ የትሮፒካል ክልል በሽታዎች፣ የተዘነጉት እና ችላ የተባሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያዘው የጤና አጀንዳ እምብዛም ትኩረት ስለማያገኙ እና በአንጻሩም የሚመደበው በጀት ያንኑ ያህል እጅግ አናሳ በመሆኑ ነው።” ሲል ይዘርዝራል።

“ለዚህም ዋናው ምክኒያት በአመዛኙ በድህነት ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦች የሚታመሟቸው የበሽታ ዓይነቶች ከመሆኑ እውነታ ጋር የተያያዘ ነው።”

እነኚህም የበሽታ ዓይነቶች በተለያዩ ጥገኛ ተውሳኮች፣ ባክቴሪያ እና የቫይረስ ዝርያዎች የሚመጡ ናቸው። የንፅህና አጠባበቅ እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት የሚያባብሷቸው ሥር የሰደዱ እና የዕለት ተዕለት ሕይወትን የሚያሰናክሉ የበሽታ ዓይነቶች ናቸው። በስፋት ከሚታዩትም መካከል፡- ዝሆኔ፣ ትራኮማ፣ በውሃ ውስጥ በሚራቡ ጥገኛ ተውሳኮች አማካኝነት የሚመጣው እና ቆዳን ሰንጥቆ በመግባት ጉበት እና ሌሎች ዋና ዋና የሰውነት አካላትን የሚያጠቃው ተላላፊ በሽታ፤ እንዲሁም አንጀት እና ሆድ ዕቃ ውስጥ የሚራቡ ጥገኛ ተውሳኮች እንደሚገኙበት ርዕሰ አንቀጹ ይዘረዝራል።

እነዚህ በሽታዎች ዛሬ ቁጥራቸው አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ በአብዛኛው በአፍሪካ፣ በእስያ እና በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ሰዎችን ያጠቃሉ። የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት እነኚህ በሽታዎች ሰለባዎቻቸውን ለምዕተ ዓመታት ለዓይነ ስውርነት እና ለተለያዩ የአካል ጉዳቶች ከመዳረጋቸውም በላይ ብዙዎችን ለህልፈት ጭምር ዳርገዋል። እንዲሁም ከትውልድ ወደ ትውልድ በግለሰቦች እና በማህበረሰቦች ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ በጣም አስከፊ እነደነበር ጠቅሶ የታዳጊ ልጆችን የአእምሮ እድገት በማቃወስ የትምህርት ቤት ምዝገባ ያስተጓጉላል፤ የአዋቂዎችንም የመሥራት እና የማደግ አቅም ይቀንሳሉ።

እንዳለመታደል ሆኖም አብዛኛዎቹ ተጠቂዎች የሕክምና እርዳታ የማግኘት ዕድል ስለሌላቸው ላልተቋረጠ የድህነት እና የበሽታዎች አዙሪት ይጋለጣሉ።

መልካሙ ዜና እነኚህ የበሽታ ዓይነቶች ከሰው ወደ ሰው መከላከል እና በቀላል ወጪም በሚገኙ መድሃኒቶች መታከም የሚችሉ መሆናቸው ነው። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በ2006 ዓም እነኚህን በሽታዎች ለመቆጣጠር የተሰባሰበውን ዓለም አቀፍ ጥምረት ተቀላቀለች።በጊዜውም የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ዓለም አቀፍ ተራዶ ፕሮግራም USAID በበኩሉ በእነኚህ የበሽታ ዓይነቶች የሚሰቃዩትን ብዙዎች ለማከም የሚያስችልና የህዝብ እና የግሉን ዘርፍ ያስተባበረ መርሃ ግብር አስተዋውቋል። መርሃ ግብሩም በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለበሽታው እንዳይጋለጡ በመለየት፣ ከመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች የተለገሱ መድሃኒቶችን በማሰራጨት እና ውጤቱን በመገምገም ላይ ትኩረት በማድረግ በመሥራት ላይ ይገኛል።

በሌላ በኩል /USAID/ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2006 ዓም አንስቶ እነኚህን ቸል የተባሉ በሽታዎች ለማጥፋት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለግሷል። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ወጭ የሚያደርጋት እያንዳንዷ ዶላር በምላሹ 26 ዶላር ለሕበረተሰብ በማስገኘት የሕክምና ዘመቻዎች በድምሩ ሃያ ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው መድኃኒት ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል።

በዚህም አማካኝነት ቁጥሩ ከ500 ሚልዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ ብርቱ ችግር ከሚያስከትሉት የበሽታ ዓይነቶች ሶስቱ ህክምናው እንዳያስፈልጋቸው ማድረግ ችሏል።

/USAID/ ከሌሎች በርካታ አጋሮቹ ጋር በመተባበር ችግሩን ለመቅረፍ እና አንድ ቀን እነዚህን ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ በሽታዎች በማስወገድ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ለማሻሻል በመሥራት ላይ መሆኑን ጠቅሶ የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ ሃተታውን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG