Accessibility links

Breaking News

ዩናይትድ ስቴትስ በሙሰኝነት በተወነጀሉ የኬንያ የቀድሞ ባለሥልጣን ላይ የቪዛ እገዳ ጣለች


ዩናይትድ ስቴትስ ጉቦ መቀበልን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የሙስና አድራጎት በመፈጸም የተወነጀሉት የቀድሞ የናይሮቢ አገረ ገዢ ማይክ ሳንኮን ዩናይትድ ስቴትስ መግቢያ ቪዛ እንዳያገኙ አግዳቸዋለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ባወጡት መግለጫ ሳንኮ ህግ ተላልፈው ጉቦ የተቀበሉት የመንግሥት የሥራ ኮንትራቶችን ለጓደኞቻቸው በማሰጠታቸው መሆኑን ማውሳታቸውን በመግለጽ የዛሬ ርዕሰ አንቀጽ ጽሁፉን ጀምሯል።

"የፈጸሙት አድራጎት" አሉ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ "የቀድሞው ባለሥልጣን የፈጸሙት የህግ የበላይነትን እና በኬንያ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ ህዝቡ ያለውን አመኔታ የሚሸረሽር ነው"

ባለቤታቸው ፕሪምሮስ ኢምቡቪ፣ ሴት ልጆቻቸው ሳሙቩ ኢምቡቪ እና ሳልማ ኢምቡቪ እና ትንሽ ልጃቸውም ጭምር በዩናይትድ ስቴትስ ቪዛ ዕገዳው ተካትተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ኦፐሬሽን እና ተያያዥ መርሃ ግብሮች ምደባ ድንጋጌ መሰረት የተወሰደው ውሳኔ ሳንኮ እና ቤተሰባቸው ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ የሚከለክል መሆኑን ርዕሰ አንቀጹ አውስቷል።

የቅርብ ጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ኬንያን አስመልክቶ ያወጣው የሰብዐዊ መብቶች ሪፖርት እንደሚያመለክተው በሀገሪቱ አሁንም ከባድ የሙሰኝነት ችግር አለ።

ያም ብቻ ሳይሆን በማናቸውም የመንግሥት አስተዳደር ዕርከኖች ያሉ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በተጠያቂነት አይያዙም ሲል ርዕሰ አንቀጹ ቀጥሏል።

እአአ በ2019 ማይክ ሳንኮ በበርካታ የሙስና ወንጀሎች ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ እና በቀጠለው ዐመት ከናይሮቢ አገረ ገዢነታቸው በከባድ ጥፋት እና በስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም ተወንጅለው መነሳታቸው ይታወሳል። እስካሁን ለፍርድ አልቀረቡም።

ቀጠለ ርዕሰ አንቀጹ፤ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ኬንያ ውስጥ ሙስናን አስመልክቶ ኬንያን ከአንድ መቶ ሰማኒያ የዐለም ሀገሮች ውስጥ 128ኛ ላይ አስቀምጧታል ካለ በኋላ ታዲያ በሙሰኝነት የተከሰሱ ሰዎች የፍርድ ቤት ሂደት አዝጋሚነት ህዝቡን እያበሳጨው ነው ብሏል።

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ሙስናን መታገል የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖሊሲ ዋና አካል አድርገውታል። ይህ ስለምን እንደሆነ ኋይት ሐውስ በግልጽ አስቀምጦታል። ዋይት ኃውስ በመግለጫው "ሙስና ህብረተሰቦችን የሚጠናወት ነቀርሳ ማለት ነው።

ህዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ የሚበላ፥ የመንግሥትን ዜጎቹን የማገ ልገል ዐቅም የሚሰልብ በሽታ ነው፣ በዜጎች መካከል በማህበራዊ በፖለቲካዊ እና በምጣኔ ሃብት ረገድ የእኩልነት ክፍተት እና መከፋፈልን ይበልጡን ያባብሳል።

ለንግድ ሥራ አመቺ ድባብ እንዳይኖር ያደርጋል፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ይሸረሽራል። ግጭቶችን ያቀጣጥላል። መንግሥት በህዝብ እንዳይታመን ያደርጋል።

ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅም ማግኛ የሚያደርጉ ከዜጎች የሚሰርቁት ቁሳዊ ሀብቱን ብቻ አይደለም፥ ሰብዐዊ ክብራቸውን እና ደህንነታቸውንም ጭምር ነው" ሲል ዋይት ኃውስ ሙስናን አስመልክቶ በመግለጫው ያተተውን ርዕሰ አንቀጹ ጠቅሶታል።

ሲቀጥልም "የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንዳሉት የቀድሞ የናይሮቢ አገረ ገዢ ማይክ ሳንኮ እና ቤተሰባቸው ላይ የተደነገገው ዕገዳ ዩናይትድ ስቴትስ ኬንያ ውስጥ ሙስናን በመዋጋት እና የህግ የበላይነትን በመደገፍ የዲሞክራሲ ተቋማቷን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ የሚያረጋግጥ ርምጃ ነው።

ባለን አቅም ሁሉ በክልሉም ሆነ በዐለም ዙሪያ ሙሰኞች በተጠያቂነት መያዛቸውን ለማረጋገጥ መስራታችንን እንቀጥላለን" በማለት ርዕሰ አንቀጹ ሀተታውን አብቅቷል።

XS
SM
MD
LG