Accessibility links

Breaking News

በየመን ሰላም እንዲሰፍን የሚደረግ ድጋፍ


ዩናይትድ ስቴትስ በየመን ከምታደርገው አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ በተጨማሪ ጦርነቱን ለማስቆም ሴቶችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አመራሮችን እና ሌሎች የተገፉ የማኅበረሰቡን ክፍሎች ያካተተ ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲመጣ ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች ይላል የዛሬ የዩናይትድ ስቴትስን አቋም የሚያንፀባርቀው ርዕሰ አንቀፅ።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን በዚህ ዙሪያ ባደረጉት ንግግር "የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ልዑክ ሀንስ ግሩንበርግ ያስጀመሩትን ሁሉን አካታች የመመካከሪያ መድረክ እናበረታታለን። ሁሉም ወገኖችም በዚህ የምክክር ሂደት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ እናደርጋለን" ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በበኩላቸው የተጀመረው የሰላምሂደት ስኬታማ እንዲሆን "የመላው የመናውያንን አመለካከት እና ቅሬታ እንዲሁም ለፍትህ እና ተጠያዊነት የሚያደርጉትን ጥሪ ያካተተ መሆን አለበት" ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የፀጥታው ምክርቤት አባል ሀገራት በየመን ላይ በተጣለው የጦር መሳሪያ ማእቀብ ዙሪያ ያለባቸውን ግዴታ የሚያስታውሰውን እና በሀገሪቱ ሰላም እንዳይሰፍን በሚያደርጉ ግለሰቦች ላይ የተጣለው የጉዞ ክልከላ እና የንብረትእገዳ በድጋሚ እንዲቀጥል የሚያደርገውን 2624 የተሰኘ የውሳኔ ሀሳብ በመቀበሉ መደሰቷን አስታውቃለች።

ከኢራን ለሁቲዎች የሚደርሰውን ህግወጥ የመሳሪያ ዝውውር ማስቆም ቀዳሚነት የተሰጠው ጉዳይ ነው። እነዚህ መሳሪያዎች ጦርነቱ እንዲባባስ፣ ቀጠናው እንዳይረጋጋ እና የየመናውያን ስቃይ እንዲቀጥል እያደረጉ ነው ብለዋል፣ አምባሳደር ቶማስ ግሪንፊልድ።

በመጨረሻም በየመን የሚታየው ሰብዓዊ ቀውስ በዓለም ዙሪያ ካሉት ቀውሶች ትልቁ መሆኑን በቅርቡ በምግብ እራስንበመቻል ዙሪያ የወጣ አሳሳቢ መረጃ መጠቆሙን ርዕሰ አንቀፁ ያስታውሳል። እጅግ አስፈላጊ የሆነው የሰብዓዊ ርዳታለማድረግም ዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ ወደ 585 ሚሊየን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር ለመስጠት መጋቢት ወር ላይ አስታውቃ የነበረ ሲሆን ይህም ዩናይትድ ስቴትስ በእርዳታ ከሰጠችው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።

ይህን ገንዘብ ጨምሮም ዩናይትድ ስቴትስ የየመን ጦርነት ከሰባት አመት በፊት ከጀመረ አንስቶ 4.5 ቢሊየን ዶላር ማውጣቷን አስታውቃለች። ሆኖም በየመን ከሚፈለገው የሰብዓዊ እርዳታ 30 ከመቶ ብቻ መሆኑን በመግለፅ ዩናይትድ ስቴትስ ሌሎች በተለይ በቀጠናው የሚገኙ እርዳታ ሰጪ ሀገራት - በየመን የሚታየውን ስቃይ ለማብቃት እርዳታ እንዲሰጡጥሪ ታቀርባለች።

ይህ እርዳታ በተለይ ህይወት ለማዳንና ስቃይን ለመቀነስ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንና በቀጥታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች መድረስ እንዳለበት የሚያሳስቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብሊንከን "ዕርዳታ እንዳይደርስ የሚያስተጓጉሉ ሁሉም ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እና እርዳታው ለሚፈለገው አካላት እንዲደርስ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

ሰብዓዊ እርዳታ ብቻውን በየመን የሚታየውን ችግር ከስር መሰረቱ አይፈታውም የሚለው የዛሬ ርዕሰ አንቀፅ፣ ሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከፀብ ጫኒነት ተቆጥበው፣ ለየመን ህዝቦች ሲሉ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መፍትሄ መምጣት ለሚችልበት መንገድ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቋል።

XS
SM
MD
LG