Accessibility links

Breaking News

ዩናይትድ ስቴትስ፡- በድርቅ ለተጠቃው የአፍሪካ ቀንድ እርዳታ


በድርቅ ከተጠቁ አካባቢዎች የሸሹ ሶማሊያውያን በሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ ዳርቻ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ እአአ ሰኔ 4/2022
በድርቅ ከተጠቁ አካባቢዎች የሸሹ ሶማሊያውያን በሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ ዳርቻ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ እአአ ሰኔ 4/2022

“በአፍሪካ ቀንድ በታሪክ ከፍተኛ የሆነው ድርቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ለአደጋ አጋልጧል፡፡” ይላል ርዕሰ አንቀጹ ሀተታውን ሲጀምር፡፡ በመቀጠልም “ዩናይትድ ስቴትስ ለከፍተኛ አደጋ ለተጋለጡት እነዚህ ሰዎች አስችኳይ እርዳታ ለመስጠት በዓለም አቀፍ የልማትና ተራድኦ ድርጅት(ዩኤስኤድ) አማካይነት ወደ 105 ሚሊዮ ዶላር የሚጠጋ የሰብአዊ እርዳታ ሰጥቷል፡፡” ብሏል፡፡

“ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሳይመጣ የቀረ የዝናብ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ በብዙ መቶሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለከፍተኛ የረሃብ አደጋ የመጋለጣቸውን እድል እየጨመረው ነው፡፡ አምስተኛው ዙር የዝናብ ወቅትም ከአማካዩ ጊዜ ያነሰ እንደሚሆን በመገመቱ ህይወታቸውን በሰብሎችና ከብቶች እርባታ ላይ በመሰረቱ ቤተሰቦች ላይ የከፋ አደጋ ደቅኗል፡፡” ያለው ርዕሰ አንቀጽ “በዚህ የተነሳ ከ16 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች አጣዳፊየሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ቁጥር ባልተለመደ መልኩ በመጭው መስከረም ጨምሮ እስከ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን እርዳታ ፈላጊዎች ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡” ሲል ተንብይዋል፡፡

ርዕሰ አንቀጹ በመቀጠል “ተጨማሪው እርዳታ የዩ.ኤስ.ኤድ አጋሮች ምግብ እንዲያቀርቡ፣ የጤናና የተመጣጠነ ምግብ አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም ንጹህ ውሃ እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል፡፡ የገንዘቡ ድጋፍ በድርቁ የተፈናቀሉ ሴቶችና ልጃገረዶች ደህንነቱ የተጠበቀበት መጠለያ እንዲያገኙና ሥራውን ለመምራት በማስቻል ያግዛል፡፡” በማለት አትቷል፡፡

“የሩሲያው ጭካኔ የተሞላበትና ያለምንም ምክንያት የተቀሰቀሰው የዩክሬኑ ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የምግብ፣ የነዳጅና የማዳበሪያ ዋጋዎች እንዲንር፣ የአቅርቦቱም እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡” ያለው የርዕሰ አንቀጹ ጽሁፍ፣ “ሩሲያ በዩክሬን ላይ በምታካሂደው መጠነ ሰፊና ሙሉ ወረራ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ እንደሚገኙ እንደ ሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ የአፍሪካ ቀንድ ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ማስመጣት ባለመቻሏ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ወንዶችና ህጻናት ምግብ የማያገኙ ከሆነ ህይወታቸው ለአደጋ እንዲጋለጥ አድርጓል፡፡ ወደ 70 ከመቶ የሚሆነው የሶማልያ እና ወደ 10 ከመቶ የሚጠጋው የኬንያ ሰብሎች የሚገኙት ከዩክሬን ነው፡፡” ብሏል፡፡

“ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካ ቀንድ በግል ትልቁን እርዳታ ከሚሰጡ አገሮች ቀዳሚዋ ናት፡፡ እኤአ 2022 ዓመት ከገባ ወዲህ በክልሉ ከ507 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ሰጥታለች፡፡” ያለው ርዕሰ አንቀጽ “ ይሁን እንጂ ከሌሎች ለጋሾች ተጨማሪ አስችኳይ የገንዘብ ድጋፎች አሁንም ያስፈልጋሉ፡፡ ካለው የድርቁ ከፍተኝነትና ከሚያስፈልገው የሰብአዊ እርዳታ መጠን አንጻር፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሌሎች ለጋሾች የሚሰጡትን እርዳታ በመጨመር ከፍተኛውን ረሀብ እንዲከላከሉና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት እንዲታደጉ ያሳስባል፡፡” ብሏል፡፡

በመጨረሻም “ዩናይትድ ስቴትስ ብቻዋን በክልሉ የሚያስፈልገውን እርዳታ ማሟላት አትችልም፡፡ ብዙ ስቃይና ብዙ ህይወትን ለማትረፍ ዓለም አቀፉ ለጋሽ ማህረበሰብ አንድ ላይ መተባበር ያለበት ጊዜው አሁን ነው፡፡” ሲል ርዕሰ አንቀጹ ሀተታውን ደምድሟል፡፡

XS
SM
MD
LG