በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ “ዛሬ ዘመናዊ መሳሪያዎች ሁሉ በእጃችን ቢኖሩም በዓለም ፈጽሞ አይቼው የማላውቀው እጅግ የከፋው የምግብ ደህንነት ቀውስ ገጥሞናል” ማለታቸውን በመጥቀስ የጀመረው ርዕሰ አንቀጽ፣ “አፍሪካ ውስጥ ከአስምት ሰዎች መካከል አንዱ ተመጣጣኝ ምግብ አያገኝም - ከአምስት አንዱ!” ብሏል፡፡
አምባሳደሯ “የምግብ ደህንነት ዋስትና እጦት ማለት ቤተሰቦች ልጆቻቸውን መመገብ አልቻሉም ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ስኬታማ እንዲሆኑ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ አልቻሉም ማለት ነው፡፡ ከዚህ የከፋ ሲሆን ደግሞ እጅግ የከፋው ችጋርና ጠኔ ማለት ነው፡፡ ችጋርና ጠኔ ማለት ሞት ማለት ነው፡፡” ማለታቸውንም ርእሰ አንቀጹ አስታውቋል፡፡
“ረሀብን ለማስወገድ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያለብን ለዚህ ነው” ያሉት ግሪንፊልድ “ያንን ለማድረግ ቀድሞውኑም የምግብ ደህንነቱን እጥረት ያመጣው ምን እንደሆነ መመልከት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
አምባሳደሯ ምክንያቶቹን ሲገልጹ “አራት ግልጽ መንስኤዎች ይታዩኛል፣ “ኢ” በተሰኘው እንግሊዝኛው ሆሄ የሚጀምር አንድ ቃልና “ሲ” በተሰኘው የእንግሊዝኛ ሆሄ የሚጀምሩ ሶስት ቃላት አድርጌ እጠራቸዋለሁ፤ እነሱም ኤነርጂ፣ ክላይሜት፣ ኮቪድ እና ኮንፊልክት ወይም በአማርኛው የኃይል ምንጮች፣ የአየር ንብረት፣ ኮቪድ እና ግጭት ናቸው፡፡”ማለታቸውን ርእሰ አንቀጹ አትቷል፡፡
“የኃይል ሰጪዎች አቅርቦት ዋጋ ባለፈው ዓመት አሻቅቧል” ያሉት አምባሳደሯ ምክንያቱም ኃይል ከምግብ ምርት ውስጥ ተነጥሎ የሚታይ ባለመሆኑ ከፍተኛ የኃይል ዋጋ ማለት ተጨማሪ የምግብ ውድነት ማለት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የመጀመሪያው ሲ climate change ወይም አየር ንብረት ለውጥ ለሚለው ቃል የቆመ ነው በማለት ማብራሪያቸውን አምባሳደሯ ሲጀምሩ፡፡
“የአየር ንብረት ቀውስ ማለት የጎርፍ ፣ የከፍተኛ ዝናብና ከፍተኛ ንዳድ የመሳሰሉ የተፈጠሮ አደጋዎች ቀውስ ውጤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ደግሞም በቀጥታም ወደ ምግብ ደህንነት ቀውስ ያመራል፡፡”
ሁለተኛው ምክንያት ሲ በሚለው እንግሊዝኛ ቃል የሚጀምረው ኮቪድ ነው መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ቶማስ ግሪን ፊልድ “ኮቪድ 19 በምግብ ስርዓቱ ላይ አስቸኳይና ተጨማሪ ድንጋጤ አምጥቶብናል፡፡ ከኮቪድ በፊት የምግብ ደህንነት ችግር የነበረባቸው 100 ሚሊዮንስ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ፣ ልክ በሶስት ወር ውስጥ ያ ቁጥር አድጎ ከ190 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ደርሷል፡፡ ” ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ከፍተኛ የረሀብ ምክንያት ነው ብዬ የማምነውና ሲ በሚለው የእንግሊዝኛ ሆሄ የሚጀምር ሶስተኛው እኩይ ምክንያት አለ፡፡ ያም በግጭት የሚፈጠረው ረሀብ ነው፡፡ ሆን ተብሎ የሚፈጠር ረሀብ፡፡ ረሀብ ለጦርነት መሳሪያነት ሲውል” ሲሉ በጽሁፍ ላይ አብራርተዋል፡፡
“እነዚህ ሁሉ ችግሮች የኃይል አቅርቦት፣ የአየር ንብረት፣ ኮቪድ እና ግጭት ተደባልቀው በህይወት ዘመናችን አይተነው ወደ ማናውቀው የከፋ ረሀብ መርተውናል፡፡” ሲሉ አምባሳደር ቶማስ ግሪን ፊልድ መናገራቸውም ተጠቅሷል፡፡
በመጨረሻም ግጭት ረሀብን እንደጦርነት መሳሪያ በመጠቀም ሰዎች ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ያስገድዳል፡፡ ይህ በአካባቢው ባሉ አገሮች መካከል የምግብ ሰርዓት ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡
አምባሳደር ቶማስ ግሪን ፊልድ “ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ ሰፋሪዎችን፣ አገር አላባ ሰዎችንና፣ በመላው አፍሪካ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ለመርዳት የሚውል፣ ከ127 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ የምግብ እርዳታ እንደሚሰጥ ማስታወቃቸውንም ርዕሰ አንቀጹ ገልጿል፡፡
በመጨረሻም “ረሀብን ለማጥፋት ከመንግስታት ጋር፣ ከአገሮችና ከህዝቦች ጋር አብሮ ለመስራት ወቅቱ አሁን ነው፡፡ ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት፣ ከግሉ ዘርፍ እንዲሁም ዳያስፖራውን ለማንቀሳቀስ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና የተሻሉ ቴክኒኮችን በመጠቀም የምግቡን ሥርዓቱንና የወደፊቱን ለመገንባት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል ሲል ርዕሰ አንቀጹ ሀተታውን ደምድሟል፡