Accessibility links

Breaking News

ድጋፍ ለኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ህዝብ


“በአፍሪካ ቀንድ የሚኖሩ ቁጥራቸው 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዎች የምግብ እጥረት አደጋ ከፊታቸው ተደቅኗል። ለአራት ተከታታይ ዓመታት ለበረታ ድርቅ የተጋለጠው ክልል የፊታችን ጥቅምት ወር ሲመጣም አምስተኛውን ይጋፈጣል።” ያለው ርዕሰ አንቀጽ በማያያዝም

“የአፍሪካ ቀንድ በዓመት ሁለት የዝናም ወራት አለው።” ሲሉ ለወትሮው በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ዝናም የሚያገኘው አካባቢ ለአራት ተከታታይ ዓመታት በድርቅ ሲመታ፣ ይህ ያሁኑ በታሪክ የመጀመሪያው መሆኑን እዚህ ዋሽንግተን ላይ ባሰሙት ንግግር ያወሱት፣ በቅርቡ በሶማሊያ እና በኬንያ በድርቁ ክፉኛ የተጎዱ ክልሎችን ጎብኝተው የተመለሱት የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት እና ተራድኦ ፕሮግራም USAID አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር የተናገሩትን በመጥቀስ የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ ይንደረደራል።

“የግጦሽ መሬቶች ወደ ደረቅ አቧራ ሜዳ ተለውጠዋል። በመጽሃፍ ቅዱስ ታሪኮች የሚወሱ ትዕይንቶችን በመሰለ ገጽታ፣ የእርሻ ሥራ ይሰሩ የነበሩ የተዳከሙ እንስሳት በበሽታ እያለቁ ነው። በእስካሁኑም በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ ቢያንስ ቁጥራቸው 7 ሚሊዮን የሚደርሱ የቤት እንስሳት በድርቁ ሳቢያ ሞተዋል። የእንሣቱን ውሃ ጥም የሚቆርጥ በቂ ውሃ ወይም የሚግጡት በቂ ሣር የለም” ብለዋል።

“የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት ላደረሰባቸው የአካባቢው ሦስት አገሮች፡ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በእጅጉ አስፈላጊ ለሆነው የሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ጠቅላላ ድምሩ አንድ ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን እርዳታ በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት እና ተራድኦ ድርጅት USAID በኩል በማቅረብ ላይ ይገኛል።በጊዜው የሚደረግ ሰብአዊ ድጋፍም ህይወትን ለማዳን ወሳኝ ነው።” ያለው ርዕሰ አንቀጽ በማከልም፣ ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሁን ቀደም ታይቶ የማያውቅ ከፍተኛ ድርቅ ህልውናቸው አደጋ ላይ ለወደቀ ቁጥራቸው ከስምንት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በጠቅላው የ668 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እያደረገች ነው።” ሲል አብራርቷል።

በኬንያም በድርቁ ሳቢያ ቁጥሩ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ ከረሃብ አፋፍ ማቃረቡን፣ አካባቢዎቻቸው በቆላማ እና ከፊል በረሃማነት ባለባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ማህበረሰቦችም በጣም ተጎድተዋል።” ያለው ርዕሰ አንቀጽ በመቀጠልም ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ 70 በመቶ የሚሆነው ሰብል ቁጥራቸው ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ከማያንስ የቤት እንስሳት ጋር መውደሙን አስታወሷል።

USAID ለሌላው በድርቁ ክፉኛ ለተጎዳው የኬንያ ሕዝብ ለአስቸኳይ የምግብ እና ሌሎች ወሳኝ የሰብአዊ የልማት ድጋፍ የሚውል የ255 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ በመስጠት ላይ መሆኑን አመልክቷል።

በሶማሊያ ደግሞ ቁጥሩ ሰባት ነጥብ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ በቀውሱ መጎዳቱን፣ ከ3 ሚሊዮን በላይ የእርሻ ሥራ የሚሰሩ እንስሳት ማለቃቸውን እና እስከ ያዝነው የአውሮፓውያኑ 2022 መጨረሻ ባለው ጊዜም አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ህጻናት በዓመቱ መጨረሻ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የመጋለጥ ዕድል ያላቸው መሆኑን ዘርዝሯል።

በተጨማሪም USAID እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ የሰብአዊ እና የልማት እገዛዎች የሚውል የ476 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለሶማሊያ ህዝብ በመስጠት ላይ ሲሆን፤ ይህም ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ ለሶማሊያ የለገሰችውን ዕርዳታ መጠን ከ707 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያደርሰው ርዕሰ አንቀጹ ጠቁሟል።

ይህ ዩናይትድ ስቴትስ በማቅረብ ላይ የምትገኘው የሰብአዊ እርዳታ አገራቸው “ለኢትዮጵያ፣ ለኬንያ እና ለሶማሊያ ህዝቦች ደህንነት” ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የተናገሩት የዩናይትድ ስቴትሷ የዓለም አቀፍ የልማት እና ተራድኦ ድርጅት አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር አያይዘውም “እየተስፋፋ የመጣውን የቸነፈር አደጋ ለመከላከል እና በሚሊዮኖች የሚሰላውን የሞት አደጋ ከወዲሁ ማስቀትረት ይቻል ዘንድ አጋሮቻችን በየፊናቸው የገቡትን ቃል በማጠናከር እንዲቀላቀሉን እናሳስባለን” ሲሉ ያሰሙትን ጥሪ ጠቅሶ የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ ሃተታውን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG