Accessibility links

Breaking News

ዩናይትድ ስቴትስ አዲሱን የሶማሊያ መንግሥት ምስረታ ደገፈች


ዩናይትድ ስቴትስ በሶማሊያ አዲስ መንግሥት በመመስረቱ ደስታዋን ገልፃ አገሪቱ ያሉባትን ችግሮች ለማስወገድ አብራ ትሰራለች ሲሉ በሶማልያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደርና በተባበሩት መንግሥታት ምክትል የዩናይትድ ስቴትስ ተወካይ ሪቻርድ ሚልስ መናገራቸውን በመጥቀስ የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ ሀተታውን ይጀምራል፡፡

ሶማሊያ ከገጠሟት ፈተናዎች መካከል በፌደራልና የፌደራላዊ አስተዳደር አባላት በሆኑ የክልል መንግሥታት መካከል መግባባትን መፍጠር፣ ፌዴራላዊ ህገ መንግሥቱን መገምገም እንዲሁም የዕዳ እፎይታውን ማስገኘት የመሳሰሉት ይገኙበታል ብሏል ጽሁፉ፡፡

“ሞቃዲሾ ውስጥ ነሀሴ 14 ቀን 2014 በሀያት ሆቴል በደረሰው አሰቃቂ ጥቃት እንደታየው አሸባሪው የአልሸባብ ቡድን የደቀነው ስጋትም በከፍተኛ ደረጃ አሳስቢ ሆኗል” ያሉት አምባሳደር ሚልስ “ጥቃቱን በጥብቅ ያወገዙ” ሲሆን “ ዩናይትድ ስቴትስ አልሸባብን ለማሸነፍ በሶማሊያ የሚመራውን ጥረት ለመደገፍ አሁንም ቁርጠኛ ናት” ማለታቸውን ገልጿል፡፡

“የሶማሊያ ብሄራዊ የደህንነት ኃይሎች አልሸባብን ከሂራን ግዛት ለማባረር ያደረጉትን የተሳካ ጥቃት እናደንቃለን፡ሽብርተኝነትን ለመዋጋት አፍሪካ ህብረት ሶማሊያ ውስጥ ላለው የሽግግር ተልዕኮ፣ ለሶማሊያ የደህንነት ኃይሎች እንዲሁም፣ በሶማሊያና በመላው ምስራቅ አፍሪካ የሰላምና የጸጥታ ጠንቅ የሆኑ የአልሻባብ ታጣቂዎችን በሽብርተኝነት የሚፈረጀውን የ751 ማዕቀብ ድንጋጌ በመጠቀም የቀጥታ ድጋፍ በማድረግ፣ በእጅ ያለን ጠቃሚ መሳሪያ ሁሉ ለመጠቀም ቁርጠኞች ነን” ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ አያይዘው፣ “ዩናይትድ ስቴትስ፣ ለሶማሊያ ከማናቸውም ከፍተኛውን ሰብዐዊ ዕርዳታ ሰጭ እንደመሆኗ ፣ ታይቶ ባልታወቀው ከባድ ድርቅ፣ የምግብ ዋስትና ችግር ለገጠማቸው፣ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምትሰጠውን ዕርዳታ በቁርጠኝነት ትገፋበታለች” ማለታቸውንም ርዕሰ አንቀጹ ጠቅሷል፡፡

በሚቀጥለው ወር የከበደ የረሃብ ቸነፈር እንደሚከሰት በቅርቡ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ሁላችንንም እርምጃ እንድንወስድ የሚያሳስበን ነው ሲሉ አምባሳደር ሚልስ መናገራቸውን ርዕሰ አንቀጹ ጠቅሷል፡፡

አክለውም የተደቀነው ረሃብ የትኛውም አገር ብቻውን ሊቋቋመው የሚችለው ፈተና አይደለም ብለዋል፡፡

“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየጨመረ የሚሄደውን የሰዎችን ህይወትና የመተዳደሪያቸውን ውድመት ለመከላከል የግድ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እስከዛሬ ታይቶ ላልታወቀው የሶማልያ ድርቅ በዚህ ዓመት የ700 ሚሊዮን ዕርዳታ ሰጥቷል፡፡

ይህ ሶማሊያ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ዕርዳታ ምላሽ ዕቅድ ውስጥ እስከዛሬ ከተቀበለቻቸው ዕርዳታዎች በሙሉ ከ70 ከመቶ በላይ ይሆናል፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ለሰብአዊው እርዳታ የሚሰጡትን እርዳታ እንዲጨምሩ እናበረታታለን” በማለት አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም “ዩናይትድ ስቴትስ የሶማልያ ህዝብ ዲሞክራሲንና የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ለመደገፍና አብሮ ለመስራት አሁንም ቁርጠኛ መሆኑዋን ትገልጻለች” በማለት የዛሬው ርዕሰ አንቀጽ ሀተታውን ደምድሟል፡፡

XS
SM
MD
LG