Accessibility links

Breaking News

የዓለም የምግብ አቅርቦትን የማሳደግ ጥረት


የባግላዲሽ ገበሬ በሥራ ላይ
የባግላዲሽ ገበሬ በሥራ ላይ

"በአሁኑ ወቅት ላለው የምግብ ቀውስ ያደረሱን በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም እንደ ዕውነቱ ከሆነ ግን የአየር ንብረትት ለውጡ በፍጥነት እያደረሰ ያለው መጠነ ሰፊ ጥፋት ምላሽ ለመስጠት ካለን አቅም በላይ እየሆነ ነው" ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ተራድዖ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር የተናገሩትን በመጥቀስ የዛሬው ርዕሰ አንቀጽ ሐተታውን ይጀምራል።

የዩኤስኤድ ዋና አስተዳዳሪ ፓወር ይህን የተናገሩት በዓመታዊ የዓለም የምግብ ሽልማት የበርላግ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

"በአሁኑ ወቅት የአየር ሙቀት እና ጎርፍ ለአጣዳፊ ዕርዳታ ከተመደበ በጀት አቅም በላይ በፍጥነት እየጨመረ ነው። የገንዘብ ወይም የምግብ ዕርዳታ በመለገስ በምንም አይነት ልንቋቋመው የምንችለውም አይደለም። አሁን የያዝነው መንገድ አያዛልቀንም።

በሚቀጥሉት አመታት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ግዙፍ የምግብ አምራች በሆኑ የተለያዩ አካባቢዎች በአንድ ግዜ ምርት ቢበላሽ ሊከተል የሚችለውን አደጋ ለመገመት እንኳን ይዘገንናል" ብለዋል።

ሆኖም ከዚህ ጨለማ መውጫ መንገድ አለ በማለት ርዕሰ አንቀጹ ሐተታውን ይቀጥላል።

እርሱም የዓለም የምግብ ሽልማትን የመሠረቱት የአረንጓዴ አብዮት አባት ተብለው የሚታወቁት የኖቤል የሰላም ተሸላሚው የአፈር ጥበቃ እና የእህል ምርት አዋቂ ባለሙያው ኖርማን በርላግ የቀየሱት ጎዳና ነው" በማለት ርዕሰ አንቀጹ አውስቷል።

"ዶክተር በርላግ ለበርካታ ዐመታት ምርምር ካካሄዱ በኋላ አዳዲስ የስንዴ እና ሩዝ ዘሮች የእስያ እና የላቲን አሜሪካን ምርት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል" ሲሉ የዩኤስኤድ ዋና አስተዳዳሪ ፓወር ማስገንዘባቸውን ጠቅሷል።

"ከዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ ጋር በተፋጠጥንበት እና ወደፊትም የአየር ንብረት ለውጡ በምግብ ምርት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት ካለፉ ተሞክሮዎች ትምህርት መቅሰም እንዳለብን ግልጽ ነው።

እነዚህን ልምዶች አሁን በዓለም ላይ ካለው ሁኔታ ጋር ማዛመድ እና ማጠናከር አለብን" ብለዋል።

"የዘረ መል ስርዓት ምርምር ለሳይንቲስቶች ጥሩውን የእህል ዘር ዐይነት በፍጥነት የመለየቱን እና የማዳቀሉን ሂደት ያፋጥንላቸዋል ይረዳቸዋል።

ዓመታት የሚወስድ የማዳቀል ሂደት በወራት ውስጥ እንዲከናወን የሚያደርግበትም ጊዜ አለ" ያሉት ሳማንታ ፓወር ዩ ኤስ ኤድ በዐለም ዙሪያ እንዲህ ላሉ ጥረቶች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

"በ1990ዎቹ ዓመታት የማሽላ ዘሮችን በስኬት በማዳቀል ድርቅን እና ስትሪንጋ የተባለውን ሰብል ተባይን የሚቋቋሙ የዘር ዐይነቶችን ለፈጠረው ለኢትዮጵያዊው ባለ እጅግ ብሩህ አዕምሮ ወጣት ሳይንቲስት ዩኤስኤይድ እና የሮኬፌለር በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ አድርገውለታል።

የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ላሉ አስራ ሁለት ሀገሮች የቀረቡት አዲሶቹ የማሽላ ዘሮች ለከባድ ድርቅ በተጋለጡ አካባቢዎች ሳይቀር ምርታቸውን በአራት ዕጥፍ አሳድገውላቸዋል" ሲሉም አስረድተዋል።

የተጠቀሱት ሳይንቲስት እአአ የ2009 የዓለም የምግብ ሽልማት ተሸላሚው ዶክተር ገቢሳ ኢጀታ መሆናቸውን ርዕሰ አንቀጹ አመልክቷል።

ዛሬም የዶክተር ገቢሳ ኢጀታን ክንዋኔ ይበልጡን በማጠናከር እየሰሩ ላሉት የአፍሪካ አዲስ ትውልድ ሳይንቲስቶች ድጋፋችንን በመስጠት ላይ ነን።

ዩኤስኤይድ ለአፍሪሴንተር፥ ለኬኒያታ ዩኒቨርስቲ እና ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ "በስትሪንጋ ተባይ የማይበገሩ" አዳዲስ የማሽላ ዘሮችን ተመራምረው እንዲፈጥሩ ወደ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ መዋዕለ ነዋይ መመደቡን ሳማንታ ፓወር መናገራቸውን አትቷል።

"የአረንጓዴው አብዮት ዋነኛው ግልጽ መልዕክት ለግብርና ምርታማነት እና መሰረታዊ ለሆኑ ምርምሮች አስፈላጊው መዋዕለ ነዋይ ከተመደበ የምግብ አቅርቦት ከምግብ ፍላጎት በበለጠ ፍጥነት ሊያድግ የሚችል መሆኑ ነው" በማለት የተናገሩትን ጠቅሶ ርዕሰ አንቀጹ ጽሁፉን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG