የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ባለፈው የአውሮፓውያኑ 2022 በዲፕሎማሲ መስክ ተሳክተው የነበሩ አራት ዋና ዋና ጉዳዮችን በዓመቱ መጨረሻ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ መዘርዘራቸውን ጠቅሶ የዛሬው ረዕሰ-አንቀፅ ሃተታውን ይጀምራል።
ብሊንከን “ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያውጀችው ጦርነት ስልታዊ ክሽፈት መሆኑን ለማረጋገጥ ዓለምን አስተባብረናል” ብለዋል።
“ዩክሬናዊያን ለአገራቸው ዲሞክራሲ፣ ሉአላዊነት እና ነጻነት በመቆም የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ እና ለዩክሬናውያን የኢኮኖሚና የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሳለጥ በደርዘን የሚቆጠሩ አጋሮችንና ሸሪኮችን በአንድ ላይ አሰባስበናል።
የጋራ ድጋፋችን፣ አሁን የተሰጠውን 1.85 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ዕርዳታ ጨምሮ፣ የዩክሬን ተዋጊዎች መልሶ ማጥቃት እንዲያደርጉና ሕዝባቸውን ነጻ እንዲያወጡ እንዲሁም አብዛኛውን ግዛታቸውን መልሰው እንዲቆጣጠሩ አስችሏል” ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከን።
ርእሰ አንቀፁ አያይዞ ብሊንከን “የቻይናን ሕዛባዊ ሪፐብሊክን በተመለከተ ከአጋሮቻችንና ሸሪኮቻችን ጋር ያለውን ስልታዊ አንድነት አፋጥነናል” ማለታቸውን አስፍሯል።
“ባለፈው ግንቦት በቻይናን ሕዛባዊ ሪፐብሊክ የተደቀነውን ፈተና ለመጋፈጥ ያለንን ስልት አብራርቼ ነበር። እነዚህም፣ በአገር ውስጥ ጥንካሬያችን ላይ መሥራት፣ ከአጋሮቻችንና ሸሪኮቻችን ጋር አንድ ላይ መሰለፍ፣ እንዲሁም ጥቅሞቻችንን ለመጠበቅና የወደፊት ራዕያችንን ለማሳካት ከቻይና ጋር መፎካከር የሚሉት ናቸው” ሲሉ አስታሠዋል።
በተጨማሪም በታይዋን የባህር ወሽመጥ ያለውን ሰላምና መረጋጋግት ለመጠበቅ፣ የቻይና ሕዛባዊ ሪፐብሊክ በሺንጃንግ እና ቲቤት የምትፈጽመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ፣ እንዲሁም በሆንግ ኮንግ የሚታየውን የመናገርና የፕረስ ነጻነት መሸርሸር ያለንን ስጋት ለመግለጽና ለምላሹም የጋራ እርምጃ ለመውስድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሸሪኮቿ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተመለከተ አሁንም በጋራ እንደቆሙ ነው ብለዋል ብሊንከን።
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የምግብ ዋስትናን፣ ጤና፣ ሃይል፣ የአየር ንብረትን እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን በተመለከተ ላሉ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ዩናይትድ ስቴትስ አጋሮቿን አንቀሳቅሳለች ብለዋል ሚኒስትሩ።
በመጨረሻም “ሰላምን ለማስፈንና ግጭትን ለማስቆም የአሜሪካንን የዲፕሎማሲ ሃይል ተጠቅመናል” ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን።
“በመካከለኛው ምሥራቅ አንድነትንና እርቅን ለመፍጠር ከእስራኤል፣ ከሞሮኮ፣ ከባህሬን፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ከግብጽ ከመጡ አቻዎቼ ጋር በመሆን በነጌቭ ጉባኤ ላይ ተሳትፌያለሁ። በእስራኤልና ሊባኖስ መካከል
ለረጅም ግዜ የነበረውን የባህር ላይ ድንበር ውዝግብ ለመፍታት ታሪካዊ ሥምምነት እንዲመጣ አድርገናል። በኢትዮጵያና በትግራይ ሃይሎች መካከል ተኩስ እንዲቆም በአፍሪካ ኅብረት የተመራውን የሰላም ውይይት ደግፈናል። ሱዳን ወደ ሲቪል መር ዲሞክራሲ ጎዳና ላይ መልሳ እንድትገባ የሥምምነት ማዕቀፍ እንዲፈጠር ረድተናል።
በየመንም ጊዜያዊ ተኩስ ማቆም እንዲፈጠር በኋላም እንዲራዘም ረድተናል” ሲሉ መናገራቸውን ረዕሰ-አንቀጹ ይጠቅሳል።
ለአዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2023 ነፃ፣ ግልጽ፣ ጸጥታው አስተማማኝ እና የበለጸገ ዓለም ለመገንባት ዩናይትድ ስቴትስና አጋሪቿ በጋራ መሥራታቸውን ይቀጥላሉ- ሲሉ ብሊንከን ተናግረዋል በማለት ረዕሰ-አንቀፁ ሐተታውን ደምድሟል።