Accessibility links

Breaking News

በሶማሊያ ረሃብን መዋጋት


"ሶማሊያ ከዚህ በፊት ባልታየና በተራዘመ ድርቅ ስትሰቃይ ቆይታለች" ሲል የዛሬው ርዕሰ-አንቀጽ ይንደረደራል፡፡ አምስት የዝናብ ወቅቶች ደርቀው አልፈዋል፣ ስድስተኛው እየመጣ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመላ አገሪቱ ረሃብ ተስፋፍቷል፡፡

አል ሸባብ የሚያደርሳቸውን የመሳሰሉ ግጭቶች እንዲሁም ከዓለም ከፍተኛ ምግብ ላኪዎች ውስጥ አንዷ በሆነችው ዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት ሁኔታው እንዲባባስ አድርገዋል ካለ በኋላ ርዕሰ አንቀጹ “ቀድሞውንም ከባድ የነበረውን ሁኔታ ይበልጡን ያባባሰው ደግሞ የኮቪድ ወረርሽኝ የፈጠረው የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር ነው" ሲል አክሏል፡፡

“በሶማሊያ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ በክብደቱ በአሁኑ ወቅት በዓለም ካሉት አሳሳቢ ከሆኑ ከማናቸውም ሰብዐዊ ሁኔታዎች እኩል ነው” ብለዋል በተመድ የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፡፡ “ኮቪድ፣ ግጭት እና የአየር ንብረት ለውጥ በአንድነት ሆነው ያንን መስማት የማንፈልገውን ቃል "ረሃብን"ወደ ሶማሊያ አምጥተውታል" ሲሉ አክለዋል ግሪንፊልድ፡፡

አያይዘውም “ረሃብ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛው ውድቀት ነው፡፡ ምግብ በተትረፈረፈባት ዓለም አንድ ማሕበረሰብ እንዳለ በረሃብ ሊሞት አይገባውም” ማለታቸውን ርዕሰ አንቀጹ አመልክቷል፡፡

ትክክለኛው ቁጥር ባይታወቅም፣ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን በረሃብ እንደሞቱ ይገመታል ሲል ይቀጥላል ርዕሰ-አንቀጹ፡፡

የተመድ የህጻናት መርጃ ዩኒሴፍ በበኩሉ "ከ5 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሶማሊያ ሕጻናት ከፍተኛ በሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው፡፡ የእርሻ መሬቶች ጾማቸውን ሲያድሩ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች አልቀዋል ይህም ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል" ማለቱን ርዕሰ አንቀጹ ጠቅሷል፡፡

እአአ ካለፈው 2022 ጀምሮ ዩናይትድ ስቴትስ ከ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ነፍስ አድን ዕርዳታ ለአፍሪካ ቀንድ ሰጥታለች፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው የተሰጠው ለሶማሊያ መሆኑን ርዕሰ-አንቀጹ አመልክቷል፡፡

አስከትሎም የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ተጨማሪ 41 ሚሊዮን ዶላር አስችኳይ ዕርዳታ በዓለም አቀፍ የልማት ዕርዳታ ወኪሉ (ዩኤስኤይድ) በኩል ለሶማሊያ ሕዝብ እንደሚሰጥ አምባሳደር ቶማስ ግሪንፊልድ ባለፈው ጥር 29 ቀን መግለጻቸውን አስታውሷል፡፡

“ባለፈው ዓመት የመደብነው ገንዘብ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአፍሪካ ቀንድ ካዋለው ውስጥ 80 በመቶውን ይይዛል፤ ይህም ሌሎች አገሮች በድምር ከሚያዋጡት አጠቃላይ ዕርዳታ 4 እጥፍ ነው፡፡ ይህ ዕርዳታም ምግብ፣ ውሃ እና መጠለያን ለሶማሊያውያን እንዲደርስ አስችሏል” ብለዋል ግሪንፊልድ በመቀጠል፡፡

“ዩናይትድ ስቴትስ ይህን ብቻዋን መከወን አትችልም፣ ይህ የጋራ ሃላፊነት ነው፣ ሰብዓዊ መሆናችንን በጋራ የምናሳይበት ነው” ሲሉ አክለዋል ግሪንፊልድ፡፡

“ለጋሾችና ዓለም በርከት አድርገው እንዲሰጡና ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጡ ዩናይትድ ስቴትስ ትጠይቃለች፡፡ ይህ ግዜ ሰብዓዊ ዕርዳታችሁን የምትለግሱበትና በችግሩ የተጎዱትን ሰዎች ሕይወት የምትቀይሩበት ነው፡፡

ምግብና የጤና አገልግሎት የምታዳርሱበት፣ ውሃና የጽዳት አግልግሎት እንዲሁም መጠለያ የምታዳርሱበት፣ ሕይወት የምታድኑበትና የሰዎች ክብር እንዲመለስ የምታደርጉበት ነው” ሲሉ ግሪንፊልድ መናገራቸውን ጠቅሶ የዛሬው ርዕሰ-አንቀጽ ሐተታውን ደምድሟል፡፡

XS
SM
MD
LG