Accessibility links

Breaking News

የጸጥታው ም/ቤት ችግር ላይ ላለው የሶሪያ ህዝብ ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ መስጠት አለበት


በሶሪያ የደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለተረጂዎች እርዳታ ሲለግስ
በሶሪያ የደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለተረጂዎች እርዳታ ሲለግስ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው ባለፈው የካቲት ወር ቱርክ እና ሶሪያ ውስጥ የደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት ከ50 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ገድሏል፡፡

ርዕደ መሬቱ ሶሪያ ውስጥ ከ6 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች የገደለ ሲሆን እስካሁን ያልተገኙ በሺዎች የተቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን በማውሳት የዛሬው ርዕሰ አንቀጽ ጽሁፉን ይጀምራል፡፡ በርካታ መንደሮች በርዕደ መሬቱ እንዳሉ መውደማቸውንም ገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዊ ረድዔት ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸኅፊው ማርቲን ግሪፊትስ ለመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ባደረጉት ገለጻ እአአ የካቲት 6 ቀን የደረሰው ርዕደ መሬት ለ12 ዓመታት በዘለቀው ጭካኔ የተመላበት ጦርነት ብርቱ መከራ የተጫናትን ሶሪያን ችግሩን ይበልጡን አክብዶባታል፡፡ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ መሰረታዊ የመጠለያ እና ሌላም ምግብ ነክ ያልሆነ ዕርዳታ ጠባቂ መሆኑን ማርቲን ግሪፊትስ ማሳወቃቸውን ርዕሰ አንቀጹ አትቷል፡፡

የተመድ የሶሪያን ህዝብ ለቀጣዩ የሦስት ወር ጊዜ ለመርዳት የሚያውለው የ397 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲሰጠው የካቲት 14 ቀን ተማጽኖ ማቅረቡን ርዕሰ አንቀጹ ጠቅሷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ተለዋጭ የልዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተወካይ የሆኑት ሮበርት ዉድ በምክር ቤታዊ ገለጻው ላይ ሲናገሩ ዩናይትድ ስቴትስ እስካሁን ለቱርክ እና ለሶሪያ ህዝብ ዕርዳታ የሚውል 185 ሚሊዮን ዶላር መመደቧን አመልክተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕርዳታ አቅርቦት በ“አል ራይ” በ“ባብ አል ሳላም” እና በ“ባብ አል ሃዋ ማቋረጫ” በኩል መንቀሳቀስ መቻሉ ጥሩ ዜና መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሶሪያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በመላዋ ሶሪያ በተለይም በሰሜን ምዕራቡ አንገብጋቢ የሆኑ አገልግሎቶችን ለመስጠት የያዙትን ጥረት አድንቀዋል፡፡

“ይሁን እና” አሉ አምባሳደር ሮበርት ዉድ “ይሁን እና በርዕደ መሬቱ በተመታው አካባቢ ያለው ሰብዐዊ ቀውስ የጀመረው ከሦስት ሳምንታት በፊት አይደለም፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ተጨማሪ ዕርዳታ እና የዕርዳታው መድረስ በተለይ በሰሜን ምዕራባዊ ሶሪያ ለዐመታት በግልጽ ይታወቅ የነበረ ከባድ ችግር ነው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አባላት ሰብዐዊ ዕርዳታው ለህዝቡ መድረሱን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተው ያሳሰቡት አምባሳደር ዉድ “የተጎጂዎችን ህይወት ለማትረፍ የሚላኩ ዕርዳታዎች በአሳድ አገዛዝ እና ሌሎችም አካላት ወዳልተላኩበት ቦታ መሆኑን የሚገልጹ አሳሳቢ ሪፖርቶች አሉ” ብለዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ “ሶሪያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ ሰብዐዊ ዕርዳታ እንዳይደርስ እያደናቀፈ ነው” የሚባለውን ውድቅ ያደረጉት አምባሳደር ዉድ “ዩናይትድ ስቴትስ ሶሪያ ላይ በጣለቻችው ማዕቀቦች ዒላማዎቿ የሶሪያን ህዝብ ከአሰርት ዐመታት በላይ ሲያሰቃዩ የኖሩ ግለሰቦች እና አካላት እንጂ ፡ ሰብዐዊ ዕርዳታ ጠባቂዎች ላይ ያነጣጠሩ አይደሉም” በማለት አስረድተዋል፡፡

የጸጥታ ምክር ቤቱ “ትኩረቱን ሶሪያ ውስጥ ባለው ሰብዓዊ ችግር ላይ ማድረጉ ተገቢ ነው” ያሉት የዩናይትድ ስቴትሱ አምባሳደር ሮበርት ዉድ “ቢሆንም ምክር ቤቱ በፖለቲካ ሂደቱም ረገድ የበለጠ ድጋፍ ለመስጠት ይችላል መስጠትም አለበት” በማለት ያሳሰቡትን ርዕሰ አንቀጹ ጠቅሷል፡፡

“ሩሲያ በዘፈቀደ በመጠየቋ ምክንያት የህገ መንግሥታዊ ኮሚቴው የሥራ ሂደት ተቋርጧል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ ሶሪያውያን በባለቤትነት የሚመሩት ሂደት እንዲጀመር ድጋፋችንን ለመስጠት ሁላችንም እንደገና ቃል እንግባ! አገዛዙም መላውን ህዝብ በሚረዳ የፖለቲካ ሂደት ዕውነተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንዲጀምር ጥሪ እናቀርብለታለን” ያሉትን ጠቅሶ ርዕሰ አንቀጹ ጽሁፉን ደምድሟል፡፡

XS
SM
MD
LG