Accessibility links

Breaking News

የዩናይትድ ስቴትስና የኢትዮጵያ ትብብር


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት በተጓዙ ወቅት ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ሲያደርጉ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት በተጓዙ ወቅት ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ሲያደርጉ

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን በቅርቡ በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት "በ21ኛው ምዕት ዓመት ለሚያጋጥሙ ፈተናዎች የሚቀርቡ አፍሪካ መር መፍትኄዎች በይበልጥ ልዩነት እያመጡ ነው" ያሉትን በመጥቀስ የዛሬ ርዕሰ አንቀፅ መልዕክቱን ይጀምራል ።

"የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም የህዝቡም ሥቃይ እንዲያበቃ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተደረሰው ፀብ የማቆም ስምምነት አፍሪካዊ አመራር ያለውን ትልቅ ሥፍራ አመልካች ከሆኑ ጉልህ ማሳያዎች አንዱ ነው" ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንክን

“የአፈሙዞች ላንቃዎች ዝም ብለዋል፤ ውጊያ በመቆሙ የሰብዐዊ መብቶች ጥሰት እየቀነሰ ነው። ለትግራይ ክልል ሰብዐዊ ዕርዳታ መግባቱን የቀጠለ ሲሆን ችግር ላይ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች በሙሉ በሚያሰኝ ደረጃ እየደረሰ ነው ። ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶችም እንዲቀጥሉ እየተደረገ ነው። ህወሃት ትጥቅ እየፈታ ነው። የኤርትራ ኃይሎች እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት አካል ያልሆኑ ሌሎች ኃይሎች እየወጡ ነው። እዚህ ስምምነት ላይ እንዲደረስ የአፍሪካ ኅብረት፥ የኬንያና የደቡብ አፍሪካ ሸምጋዮች በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ በቁርጠኝነት ያካሄዱት የዲፕሎማሲ ጥረት መሠረታዊውን ሚና ተጫውቷል። ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆኑን ለማረጋገጥም የአፍሪካ ህብረት የቁጥጥር ወዋቅር ቁልፍ ሚና አለው ።”

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንክን "ሁለቱ ወገኖች በጦርነቱ የጭካኔ አድራጎቶች መፈፀማቸውንና አድራጎቶቹ ያደረሱትን አውዳሚ ውጤት አምነው በመቀበል ያሳዩትን ቁርጠኛነት በደስታ ተቀብለነዋል" ያሉትን ርዕሰ አንቀፁ በማስከተል ጠቅሶታል።

“ዘላቂ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ሁሉም ወገኖች የጭካኔ አድራጎቶች መፈፀማቸውን ማመናቸው ወሳኝ እርምጃ ነው። ኢትዮጵያዊያን ዕርቀ ሰላምንም ተጠያቂነትንም የሚያካትት አሣታፊና አጠቃላይ የሽግግር ፍትኅ ሥራ ላይ ለማዋል የገቡትን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል፥ በኦሮሚያም ሆነ በየትኛውም አካባቢ የፖለቲካና ጎሣ ተኮር ሁከቶች አዙሪት ይሰበር ዘንድ ብቸኛው መንገድ መርዛም የፖለቲካ ቁርሾዎችንና ብሄረሰብን መሠረት ያደረጉ ክፍፍሎችን ማሸነፍ ነው። ዩናይትድ ስቴትስም ይህ እንዲሆን በሚደረግ ጥረት አጋር እንደመሆኗ የቴክኒክም የገንዘብም ድጋፍ በመስጠት ላይ ነች።”

የሆነ ሆኖ “ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተደቀኑባት አጣዳፊ ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ዘላቂ ሰላም ለመመሥረት የሚደረገውን ጥረት ይበልጡን እያወሳሰቡት ነው” ያሉት ብሊንክን

“ዩናይትድ ስቴትስ የምግብ ዋስትናንና ሌሎችም ጉዳዮችን በሚመለከት ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት መሥራቷን ትቀጥላለች” ያሉትን ርዕሰ አንቀፁ አስከትሎ ጠቅሷል።

“የህዝቡን ጤና በመጠበቅ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለን። ለበርካታ ዓመታት በአጋርነት ያካሄድነውን ፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ ትግል መሠረት አድርገን አሁንም የኮቪድ አሥራ ዘጠኝ ወረርሽኝን አብረን እንዋጋለን። ወደፊት ለሚከሰቱ ወረርሽኞችም አስፈላጊውን ዝግጅት እናደርጋለን። በየዓመቱ ለጤና፥ ለኢኮኖሚ ዕድገት፥ ለትምህርት፥ ለዲሞክራሲና ለምግብ ዋስትና የሚውል በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር መዋዕለ ነዋይ በመመደብ የኢትዮጵያን ምጣኔኃብት መደገፋችንን እንቀጥላለን። ፍልሰተኞችንና ስደተኞችን፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሰለባዎችን መርዳታችንንም እንቀጥላለን።

"በምናደርገው ሁሉ ዓላማችን የህዝባችንን ምኞት ዕውን ማድረግ እንችል ዘንድ በዩናይትድ ስቴትስና በኢትዮጵያ መካከል ጠንካራ አጋርነት መመሥረት ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንክን የተናገሩትን ጠቅሶ የዛሬው ርዕሰ አንቀፅ መልዕክቱን አጠቃልሏል።

XS
SM
MD
LG