Accessibility links

Breaking News

ረሃብን ለማጥፋት - በግብርናው ዘርፍ ያለውን በጾታዎች መካከል ያለ ልዩነት ማጥበብ


“በቅጥር ሥራ ከሚተዳደሩ ሶስት ሴቶች አንዷ በግብርና ዘርፍ ወይም ከግብርና ጋር በተዛመደ ሥራ ላይ ነው የተሰማራችው። ይሁን እንጂ በአለም አቀፍ ደረጃ ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው ሴት እና ወንድ አርሶ አደሮች በሚያመርቱት ምርት መጠን የ24 በመቶ ልዩነት መኖሩን የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO ይፋ ያደረገው አንድ አዲስ ሪፖርት አመላክቷል።” ሲል የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ ይንደረደራል።

ለዚህም ምክንያቱ በበርካታ አገሮች በፆታ ላይ የተመሰረቱ አድሎአዊ ድርጊቶች ሴቶች ለግብርና ምርት ዘርፍ እኩል አስተዋጽኦ እንዳያደርጉ ስለሚያደናቅፋቸው መሆኑን ያመለከተው የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ፤ አያይዞም “ሴቶች ወንዶች ከሚከፈላቸው 20 በመቶ ያነሰ ክፍያ እንደሚያገኙ፤ የወንዶችን ያህል የመሬት ይዞታ ድርሻ እንደሌላቸው እና ጥራት ያለው ዘር፣ እንዲሁም እንደ መስኖ እና ማዳበሪያ የመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮች እንደማያገኙም ገልጿል። “አድልኦ የሚያደርጉ ህግጋትና አሰራሮች ተጨማሪ እንቅፋት ሆነውባቸዋል።” ሲልም ዘገባን ሪፖርቱን ዋቢ በማድረግ ይዘረዝራል።

በአንጻሩ የምግብ ዋስትና እጦት እየጨመረ በመጣበት፤ በእርሻ ምርታማነት ረገድ በሁለቱ ፆታዎች መካከል የሚታየውን ልዩነት ማጥበብ እና በግብርናው ዘርፍ ያለውን የክፍያ መጠን ልዩነት መቅረፍ፣ የአገሮችን አጠቃላይ የገቢ መጠን በአንድ ትሪሊየን ዶላር ሲጨምር፡ ለምግብ ዋስትና ዕጥረት የሚጋለጡትን ሰዎች ቁጥር ደግሞ በ45 ሚሊዮን እንደሚቀንስ አመልክቷል።

“[ሴቶች] አነስተኛ ግብአቶችን ስለሚጠቀሙ የሚያመርቱት ምርት መጠንም በአንጻሩ አነስተኛ ነው። ነገሩ ያን ያህል ለመረዳት የማያዳግት ነው።” ሲሉ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2011 የዓለሙ የምግብ ፕሮግራም ዘገባ አጠናቃሪ ያሉትን ዋቢ ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ አለም አቀፍ ተራድኦ ፕሮግራም USAID አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በበኩላቸው "በግብርናው ዘርፍ የሴቶች ሁኔታ" በሚል ርዕስ FAO ሪፖርቱን እዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ ባሰሙት ንግግር “ከዚያ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ መሻሻሎች ቢዘገቡም በአጠቃላይ የታየው ውጤት ግን በቂ አይደለም።” ብለዋል።

“ተጨባጭ ለውጥ ማየት የምንሻ ከሆነ፣ ያሉትን ሥርዓታዊ እንቅፋቶች ለመፍታት ጥረታችንን በእጥፍ ማሳደግ አለብን። ሴቶች የመሬት ባለቤትነት እንዳይሆኑ ወይም የባንክ ደብተር እንዳይኖራቸው የሚከለክሉትን ህጎች እና ብሎም ሴቶች በሕፃናት እንክብካቤ እና የቤት ውስጥ ሥራ እንዲገደቡ የሚደነግጉ ልማዶችም ማስቀረት አለብን።” ያሉት ፓወር በተጨማሪም፡ በእንግሊዝኛው ምሕጻረ ቃል GROW የሚል ሥያሜ የተሰጠውን እና ፈተናዎችን “የመቋቋም አቅም እና የተጠቃሚነት እድል ለሴቶች” የተባለ ውጥን አስተዋውቀዋል። በዚህ አዲስ እቅዳቸው አማካኝነትም ድርጅታቸው USAID ከዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ለግብርና እና ለምግብ ለሴቶች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በእጥፍ በማሳደግ ወደ 335 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያደርሰው መናገራቸውን ርዕሰ አንቀጹ ጠቅሷል።

“የዘር እና የማዳበሪያ ዋጋን እንዳይቀመስ ያደረገው የምጣኔ ሃብት ውድቀት ያስከተለውን ከፍተኛ ጫና የመቋቋም አቅም ያጎለብቱ ዘንድ ሴቶችን እንረዳለን። ከግብርናው ዘርፍ ውጭ ባለው ኢኮኖሚ መስክ ሁነኛ ሚና መጫወት ይቻላቸውም ዘንድ ሰብአዊ ቀውስ ባለባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ሴቶች ድጋፍ በቀጥታ እንዲደርስ እናደርጋለን።” ብለዋል።

ፓወር አያይዘውም GROW የተባለው ይህ አዲስ ውጥን ሴቶች በግብርና እና በምግብ ዘርፉ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳተፉ ወይም እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚከለክሉ ሕጎችን ጨምሮ ያሉትን እንቅፋቶች በሙሉ ለመፍታት የሚያግዙ አስፈላጊ ድጋፎች ይሰጣል” ማለታቸውን ያስታወሰው የዕለቱ ርዕሰ አንቀጽ “ከመንገዳቸው ላይ የተደነቀኑትን እንቅፋቶች ብናነሳ፤ ረሃብን ለማስወገድ ለሚደረገው ትግል ዝግጁ እና ፈቃደኛ የሆኑ፤ ብሎም በተጨባጭ መርዳት የሚችሉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶች አሉ።” ሲሉ አስተዳዳሪዋ የተናገሩትን ጠቅሶ ሀተታውን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG