Accessibility links

Breaking News

ጁንቲንዝ መጀመሪያ በታሰበበት የቴክሳሱ ጋልቭስተን ከተማ ተከበረ


ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዛሬ ሰኞ፣ በፌደራል ደረጃ የጁንቲንዝ በዓልን እያከበረች ትገኛለች። በዓሉ ስያሜውን ያገኘው፣ በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት እ.አ.አ በሰኔ 19 (ጁን 19) 1865 ዓ.ም ማብቃቱን ተከትሎ የአሜሪካ ወታደሮች በቴክሳስ ግዛት በሚገኘው ጋልቭስተን ደሴት ደርሰው፣ በባርነት አገዛዝ ስር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ነፃ መሆናቸውን ካሳወቁበት እለት ነው።

በሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች በባርነት ጭቆና ስር የነበሩ ሰዎች ቀደም ብለው ነፃ የተደረጉ ቢሆንም፣ በቴክሳስ ግዛት ግን ሠራዊቱ እስኪደርስ ድረስ በባርነት ቆይተዋል።በጋልቭስተን ከተማ የጁንቲንዝ በዓል አከባበር የጀመረው ከቀናት ቀደም ብሎ በተለያዩ ሽርሽሮች፣ ሰልፎች እና የሙዚቃ ድግሶች ነው።

ጁንቲንዝ በዋናነት የጥቁር ባህል እና ለአጠቃላይ የአሜሪካ አኗኗር ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚከበርበት እለት ሲሆን፣ የበዓሉ አዘጋጅ ሳም ኮሊንስ ልዩ ቁምነገሩ ግን በታሪኩ ላይ የተመሰረተ ነው ይላሉ። በጋልቭስተን መኻል ከተማ የሚገኘው እና 460 ስኩዌር ሜትር ቁመት ያለው የግርግዳ ላይ ስዕልም ጀነራል ጎርደን ግራንገርን፣ በአብዛኛው ጥቁር የነበሩትን ወታደሮቻቸውን እና ነፃ የወጡትን ሰዎች እንደሚዘክርም ይገልፃሉ።

"በደሴቱ ላይ ወደ አንድ ሺህ ሁለት መቶ የሚጠጉ በባርነት የተያዙ ሰዎች ብቻ ነበሩ" ያሉት ኮሊንስ፣ "በጁንቲንዝ ከደሴቱ የተላለፈው መልዕክት ከተሰራጨ በኃላ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ የሚበልጡት ሰዎች እና በቴክሳስ ውስጥ በባርነት የኖሩት በሚሊየን የሚቆጠሩ ስዎች በጋልቭስተን የተከሰተውን የቃል ታሪክ በሕይወት ጠብቀው አቆይተዋል" ይላሉ።

ጁንቲንዝ ለብዙ አፍሪካ አሜሪካውያን ጥልቅ ስሜታዊ ትስስር ያለው ቢሆንም በቴክሳስ ቤይታውን ከተማ ነዋሪ እንደሆነው ሮኒ ሆል አንዳንድ ነጮችም ይደግፉታል።

"እንደማስበው፣ ለጥቁር ህዝቦች ብቻ የተጀመረ በዓል ቢሆንም እያደገ መጥቷል" የሚለው ሆል፣ ጁንቲንዝን በደምብ እንደሚያከብር ይናገራል።

በደሴቱ ከተካሄዱ የጁንቲንዝ በዓል ዝግጅቶች ይልቅ በባህርዳርቻዎቹ ላይ ይዝናኑ ይነበሩ ሰዎች ቁጥር የሚበልጥ ቢሆንም፣ አንዳንድ ነዋሪዎች እና ጎብኚዎች ግን በጁንቲንዝ የተካሄደውን ሰልፍ ተካፍለዋል። ለምሳሌ የዩናይትድስቴትስ የቀድሞ ሰራዊት አባል የሆኑት ታህዋን ፓርሰን ከሉዚያና ግዛት ጁንቲንዝን ለማክበር የመጡ ሲሆን "የተከሰተውን ነገር ማስታወስ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ያለፈው ነገር የማንነታችን መገለጫ መሆን የለበትም።

ይሄን ጊዜ በጋልቭስተን ውስጥ፣ በሰዎች የተገኘውን ነፃነት ለማክበር ብቻ ሳይሆን ወደፊት ነፃነታችንን ጠብቀን ለማቆየት እራሳችንን የምናስታውስበት አርገን ልንጠቀምበት ይገባል" ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

ፓርሰን አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ ባርነትን ጨምሮ፣ የሚረብሹ የታሪክ ገፅታዎችን ለመደበቅ የሚያደርጉት ሙከራ ያሳስባቸዋል።

ኮሊንስ በበኩላቸው "እውነትን ለመናገር የዚችን ሀገር መሰረት፣ እውነትን በመናገር እና በታሪኮቹ ውስጥ ያሉትን እውነተኛ ታሪኮች በማውጣት የመጠገን ሀላፊነት አለብን። ምክንያቱም የምንድነው እውነትን በመናገር ነው" ሲሉ እንደ ጁንቲንዝ ያሉ ታሪካዊ በዓላት እውቀት፣ ሀገሪቷ ያጋጠማትን ጫፍ እና ጫፍ ያሉ ተቃራኒ የፖለቲካ አመለካከቶችን ለመቀነስ ይርዳል ይላሉ።

አንዳንድ ሰዎች አስተማሪዎች በባርነት ላይ ማተኮራቸው ከሀገር ፍቅር ይልቅ ጥፋተኝነትን ያበረታታል ብለው ያስባሉ የሚሉት ኮሊንስ፣ ይልቁንም እውነተኛ የታሪክ መግለጫ ሀገሪቱን ጠንካራ እንደሚያደርገው ገልፀው ይከራከራሉ።

XS
SM
MD
LG