“የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እኤአ ከህዳር 7 ጀምሮ እስራኤልና እና አብዛኛውን መካከለኛው ምስራቅ ለዘጠነኛ ጊዜ እየጎበኙ ነው ።” ይላል ርዕሰ አንቀጹ ሀተታውን ሲጀምር፡፡
ብሊንከን በቴል አቪቭ ከእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት “ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው- ታጋቾቹን ወደ ቤታቸው ለመመለስ ፣ ለተኩስ ማቆም እና ሁሉንም ሰው የተሻለ ሁኔታ ላይ እንዲሆን ለማድረግ ብሎም ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ለማምጣት ይህ መንገድ ምናልባትም የተሻለውና የመጨረሻው እድል ነው።” ማለታቸውንም ርዕሰ አንቀጽ ጠቅሷል፡፡
ብሊንከን "እዚህ የመጣሁት ፕሬዝዳንት ባይደን ባዘዙት መሰረት የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አካል በመሆን ይህንን ስምምነት መስመር ለማስያዝና እና አንድ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ለማድረስ ነው። አሁን የሚጠናቀቅበት ጊዜ ነው። ማንም ወገን ይህንን ሂደት ሊያደናቅፉ የሚችሉ እርምጃዎችን እንዳይወስድ ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ስለሆነም የተባባሰ ሁኔታ እንዳይኖር፣ የሚባባስ ትንኮሳ እንዳይፈጠር ፣ከዚህ መስመር ሊያወጡን የሚችሉም ሆነ ግጭቱን ወደ ሌላ ቦታ አዛምተው ሊያባብሱ የሚችሉ ድርጊቶች በምንም ዓይነት መንገድ እንዳይኖሩ ለማረጋገጥ እየሰራን ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከን “ይህ በእስራኤል ውስጥ ከኢራን ከሄዝቦላህ እና ከሌሎች ምንጮች የሚመጡ ጥቃቶች ሊኖሩ ስለሚችሉበት ሁኔታ ጥልቅ ስጋት ያየለበት ወቅት ነው” ሲሉ መናገራቸውን የጠቀሰው ርዕሰ አንቀጹ “ኢራንም ሆነች ሂዝቦላህ በሊባኖስ እና በቴህራን በተፈፀሙት የታጣቂ መሪዎች ግድያ ምክንያት እስራኤልን ለመምታት ዝተዋል። ይህ የበለጠ ሰፊ ግጭት ሊኖር የመቻሉን እድል አሳድጎታል” ብሏል፡፡
“በምላሹ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ሚሳዬል ተሸካሚ ሰርጓጅ መርከብን ወደ መካከለኛው ምስራቅ አሰማርተዋል፡፡” ያለው ርዕሰ አንቀጽ፣ የአየር ኃይል መሣሪያና ቡድኖች የተቀናጁበትን አብርሃም ሊንከን የተባለውን የዩናይትድ ስቴት የባህር ኃይል ቡድንን ወደ አካባቢው ማሰማራቱን አፋጥነዋል።” ብሏል፡፡ በተጨማሪም በልክሌይ እና ሩዝቬልት የተሰኙ ሁለት ትላልቅ የባህር ኃይል ጦር መርከቦች (ዲስትሮየርስ”) በአካባቢው ለበርካታ ሳምንታት ቆይተዋል ሲል ርዕሰ አንቀጹ ጽፏል፡፡
በመጨረሻም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አነቶኒ ብሊንከን የጉብኝታቸው ትኩረት ታጋቾቹን ወደ ቤታቸው መመለስ እና የተኩስ አቁም መፈጸሙን ማረጋገጥ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል ያለው ጽሁፍ፣ ብሊንከን “ሁሉም ሰው ወደ ይሁንታ የሚደርስበት እና የማይሆንበትን ሰበብ ላለመፈለግ ጊዜው አሁን ነው።"ብለዋል ሲል ርዕሰ አንቀጹ ሀተታውን ደምድሟል፡፡