Accessibility links

Breaking News

የማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን - 2021


የደቡባዊቱን ግዛት የአላባማን ባፕቲስት ቄስ፤ ለውጥ ያለአመፅ እንዲመጣ አበርትተው የታገሉትን የሲቪል መብቶች ንቅናቄ መሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ጁኒየር)ን በወርኃ ጃንዋሪ በሦስተኛው ሣምንት በክብር እንዘክራለን።

ከዶክተር ኮንግ ትግል ታላላቅ ስኬቶች መካከል በ1964 ዓ.ም. (በዚህ ርዕሰ አንቀፅ ውስጥ ዘመን የተጠቀሰው እ.አ.አ. ነው) የወጣው በሥራ ቅጥር ወቅት ይፈፀም የነበረውን የዘር መድልዎ፣ በህዝባዊ ሥፍራዎች ይፈፀም የነበረውን ልዩነትና ማግለል ህገወጥ ያደረገው አዋጅና በዓመቱ በ1965 ዓ.ም. የወጣው ድምፅ የመስጠት መብትን ያረጋገጠ አዋጅ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሁለት ድሎች በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለምም ታላቅ ተፅዕኖን አሳድረዋል።

ምንም እንኳ የዘር መድልዎና የፍትኅ መጥፋትን ለማስወገድ የተካሄደው የዶ/ር ኪንግ ትግል በዓለምአቀፍ ህግ እስከማስቀረፅ ባይዘልቅም ቃሎቻቸውና ተግባሮቻቸው ግን በመላው ዓለም ከቅኝ አገዛዝ፣ ከአፓርታይድና ከዘር መድልዎ ጋር ይተናነቁ ለነበሩ ወንዶችና ሴቶች ታላቅ የአዕምሮና የልቦና መነቃቃትን መፍጠር ችሏል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያለው ዘመን በቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ማብቃት ተለይቶ ይታወቃል። ከ1945 ዓ.ም. እስከ 1960ዎቹ መጀመሪያ በነበሩት ዓመታት ከቅኝነት የተላቀቁ ሃገሮች ብዛት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ 115 እንዲደርስ አድርጓል። ከአባላቱ 75 ከመቶ የሚሆኑት በአድሏዊ ህግጋትና ፍትኅ የለሽ አድራጎቶች ውስጥ ሲማቅቁ የኖሩ በማደግ ላይ ያሉ ሃገሮች ህዝቦች ናቸው።

የአዳዲሶቹ መንግሥታት ተጠሪዎች በዶ/ር ኪንግ ሰላማዊ ተቃውሞና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሲቪል መብቶች ድንጋጌ መውጣት ላይ ባሳረፈው ቀጥተኛ ጫና ተነቃቅተዋል። ምንም እንኳ ቅድሚያዎቻቸው በኢንዱስትሪ ከተራመዱት ሃገሮች በእጅጉ የተራራቀ ቢሆንም ትግላቸውን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍቻ ወደሆነው የመንግሥታቱ ድርጅት መድረክ እየያዙ ዘለቁ። ልዑካኑ በቁጥር የበዙ፣ ንግግሮችና ክርክሮች እንዲነሱና እንዲካሄዱ ማድረግ የቻሉ፣ የዘር መድልዎና ፍትኅ አባልነትን ለመታገልም አንድ የሆኑ ናቸው። በውጤቱም በ1965 ዓ.ም. ሁሉም ዓይነት የዘር መድልዎ እንዲወገድ ያወጀው ዓለምአቀፍ ስምምነት እንዲወጣና እንዲፀድቅ አስችሏል።

በተከተለውም ዓመት፤ በ1948 ዓ.ም. ከወጣው የሰብዓዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ድንጋጌ በኋላ ዋናዎቹ ናቸው የተባሉት የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለምአቀፍ ስምምነትና የምጣኔኃብትና የማኅበራዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ድንጋጌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀድቀው ወጡ።

“በአርነት ታሪክ እጅግ ግዙፍ ስኬቶች የተመዘገቡበት የነፃነት ንቅናቄ በድፍን ዓለም እንደትኩሳት ተለቀቀ፤ ተስፋፋ። ቁጥሮቻቸው እጅግ የገዘፉ ብዙኃን በዘሮቻቸውና በሃገሮቻቸው ላይ ይካሄዱ የነበሩ ብዝበዛዎች እንዲያከትሙ ቁርጠኛ አቋም ያዙ” ብለዋል ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በ1964 ዓ.ም. የኖቤል የሰላም ሽልማትን በተቀበሉበት መድረክ ላይ ባሰሙት ዲስኩር። ያ መድረክ በዓለም ዙሪያ ስላለው ፀረ-ዘር መድልዎ ትግል ከተናገሩባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች አንዱ ነበር። “አሁን የምናየው - አሉ ኪንግ ያኔ - የነፃነትን መቀጣጠል ነው።

XS
SM
MD
LG