በየመን የተከሰተው ሰብአዊ ቀውስ፣ በአለም ዙርያ ካለው የከፋ ነው ተብሎ ይታመናል። በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ልጆችን ያካተቱ፣ ሃያ ሚልዮን የሚሆኑ ስዎች፣ ረድኤት ያስፈልጋቸዋል ይላል፣ የዕለቱ ርዕሰ-አንቀጽ ሀተታውን ሲጀምር።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ በቅርቡ በተደረገ የለጋሾች ጉባኤ ሲናገሩ፣ ሀገራቸው የበኩልዋን አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ ቁርጠኛ መሆንዋን ገልጸዋል።
“ወደ $191 ሚልዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ሰብአዊ ረድኤት ከዩናይትድ ስቴትስ እንደሚሰጥ ሳስታውቅ በደስታ ነው። በያዝነው 2021 አም ያበረከትነው ገንዘብ ከ $350 ሚልዮን ዶላር በላይ ደርሷል። የመን ውስጥ ከስድስት አመታት በፊት ቀውሱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዩናይተድ ስቴትስ ለየመን ህዝብ ያቀርበችው እርዳታ ከ $3.4 ቢልዮን ዶላር በላይ ይሆናል።” ብለዋል።
ይህ ገንዘብ የዩናይተድ ስቴትስ አጋሮች፣ ምግብን፣ ትምህርትን፣ መጠለያን፣ የጤና አገልግሎትን፣ ውሀን፣ የንጽህናና የደህንነት ጥበቃን እንዲሁም በተመጣጣኝ ምግብ እጦት ምክንያት የሚከስቱ በሽታዎችን ለማስወገድና ለማከም የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን እንዲያገኙ ይረዳል።
በመሰረቱ የመን ያለው ሰብአዊ ቀውስ ሊቆም የሚችለው፣ ጦርነቱ ሲያከትም ብቻ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ ሰላማ የማምጣት ጥረትዋን እያጠናከረች ያለችችውም፣ ለዚህ ነው ብለዋል ብሊንከን ።
“በፖሊሲያችን ለየምን ህዝብ ደህንነት ቅድሚያ ለመስጠት ቆርጠን ተነስተናል። ሑቲዎች በሚልም በሚታወቁት የአንሳላራላህ መሪዎች ላይ ጫና ማድረጉንም እንቀጥላለን። ሑቲዎች የጦርነቱን እድሜ እያራዘሙ ያሉትን ድንበር ዘለል ጥቃቶችንና ወታደራዊ ወረራዎችን እንዲያቆሙ ጥሪ እናደርጋለን። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚመራውን ሂደትና የድርጅቱ ልዩ ልኡክ ማርቲን ግሪፊትስ ተኩስ እንዲቆም፣ የሰብአዊ ተደራሽነት እንዲኖር እንዲሁም የሰላሙ ንግግር እንዲቀጥል የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን።” ብለዋል።
የዩናይተድ ስቴትስ ልዩ የየመን ልኡክ ቲም ሊንደርኪንግ፣ የሳውዲ አረብያና የየመን መንግስታት፣ በየመን ለሚካሂደው ግጭት መፍትሄ ለማግኘት ቁርጠኞች ናቸው ብለዋል። አሁን ሁቲዎችም ተመሳሳይ ቁርጠኛነት ማሳየት ይኖርባቸዋል።
ሑቲዎች ማሪብ በተባለችው፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች በተጠለሉባት ከተማ ላይ የሚያደርሱትን ቀጣይ ጥቃት አቁመው፣ ወደ ሰላም የሚያመራ ገንቢ ጥረት እንዲያደርጉ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ጥሪ ታቀርባለች ይላል ርዕሰ አንቀጹ።
የሰላሙ ንግግር በአፋጣኝ ቀጥሎ፣ በየመን የሚካሄደውን ግጭት እንዲያቆም፣ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል አንቶኒ ብሊንከን። የተረጋጋች፣ የበለጸገች፣ ዜጎችዋ መልሰው ለመቋቋም የሚችሉባት እንዲሁም የተሻለ መጻኢ እድል ያላት የመን እንድትኖር፣ ግፊት የሚደረግበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉም፣ የዩናይተድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ማከላቸውን፣ የዛሬው ርእሰ-አንቀጽ ጠቅሶ፣ ሀተታውን አብቅቷል።