Accessibility links

Breaking News

የሴቶች የመምረጥ መብት 100ኛ ዓመት - በዩናይትድ ስቴትስ


በዩናይትድ ስቴትስ 19ኛው የህገ መንግሥት ማሻሻያ የተደነገገበት 100ኛ ዓመት መታሰቢያ እአአ ነሃሴ ሃያ ስድስት እየተከበረ ነው።

19ኛው የህገ መንግሥት ማሻሻያ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ፆታን መሠረት አድርጎ ዩናይትድ ስቴትስ ደረጃም ይሁን በማናቸውም ክፍለ ግዛቶቿ ሊከለከል ወይም ሊገደብ አይችልም ብሎ ደንግጓል።

ይህ የህገ መንግሥት ማሻሻያ የተደነገገ ዕለት እነሆ ሃያ ስድስት ሚሊዮን አሜሪካውያን የሃገራቸውን የወደፊት ጉዞ በተመለከተ በሚወሰዱ ውሳኔዎች ለመሳተፍ በቁ በማለት የዛሬው ርዕሰ አንቀጽ ጽሁፉን ጀምሯል።

የሴቶች የመመረጥ መብት ንቅናቄ በይፋ የተጀመረው እኤአ በ1848 በተካሄደው የመጀመሪያ ጉባዔቸው ነበር፤ ከዚያ በቀጠሉት ሰባ ዓመታት የንቅናቄው አባላት ወንዶችም ሴቶችም ነበሩ። የሴቶች የመምረጥ መብት በህግ እንዲፈቀድ በቻሉት መንገድ ሁሉ ሲሞክሩ ቆዩ፣ ይህን መብት የሚያረጋግጥ የህገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲወጣ ረጅም እና አድካሚ ትግል አካሂደዋል ሲል ርዕሰ አንቀጹ አስታውሷል።

ይህን ትግላቸውን እያካሄዱ በመሃሉ አንዳንድ ሴቶች በህገ ወጥ መንገድ በምርጫ ድምጽ ለመስጠት ሲሞክሩ፣ ሙከራቸው ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ ዳኞች ከጎናችን ይቆሙልናል ብለው ተስፋ በማድረግ በፍርድ ቤት ክስ ይመሰርቱ ነበር።

ይህ ዘዴ ሲከፍባቸው ደግሞ በክፍለ ግዛት ደረጃ እንቅስቃሴያቸውን ጀመሩ እናም የተሻለ ስኬት አገኙ።

19ኛው የህገ መንግሥት ማሻሻያ በጸደቀበት ጊዜ ከዚያ ቀደም ብለው ከሀገሪቱ ክፍለ ግዛቶች ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት ለሴቶች የመምረጥ መብት ሰጥተው ነበር።

የህገ መንግሥት ማሻሻያው ኮንግሬስ ውስጥ በተጓተተ መንገድ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ እአአ1919 ሰኔ ወር ላይ በቂ የድጋፍ ድምጽ አግኝቶ ለማለፍ በቃ። ቴኔሲ ክፍለ ግዛት ማሻሻያውን ያጸደቀች የመጨረሻዋ ክፍለ ግዛት እንደነበረች ርዕሰ አንቀጹ አስታውሷል።

የሴቶች የመምረጥ መብት ትግል ግንባር ቀደም መሪዎች ከነበሩት አንዷ ሱዘን ቢ አንተኒ በ1873 ያደረጉትን ድንቅ ንግግር ሲያዘጋጁ የሴቶች የመምረጥ መብት መከበር እንደሚገባው ለመሟገት የህገ መንግሥቱን መቅድም መሰረት እንዳደረጉት ርዕሰ አንቀጹ አውስቷል።

እንዲህም ይላል

“እኛ የዩናይትድ ስቴትስ ህዝብ ይበልጡን ፍጹም አንድነት እንመሰርት ዘንድ ፍትህ እናሰፍን። የሃገር ጸጥታ እንገነባ ዘንድ የጋራ መከላከያ እና ሁለንተናዊ ደኅንነት ይኖረን ዘንድ፥ ደግሞም የነፃነታችን በረከት ለራሳችን አልፎም ለመጪው ትውልዳችን ይተርፍ ዘንድይህንን የዩናይትድ ስቴትስ ህገ መንግሥት ሰይመናል፣ ደንግገናል።"

እናም አሉ ሱዘን ቢ አንተኒ ህገ መንግሥታችን ይህን አንድነት የመሰረትን የዩናይትድ ስቴትስ ህዝብ አለ እንጂ ነጮቹ ወንዶቹ ዜጎቿ ወይም ወንዶቹ ዜጎቿ አላለም፥ ደግሞም የነፃትን በረከት ሴቶቹንም ጨምሮ ለህዝቧ ሁሉ ለማረጋገጥ አለ እንጂ ለገሚሱ ህዝቧ ከመጪው ትውልድም ለገሚሱ እንዲተርፍም አላለም" ብለው ሱዘን ቢ አንተኒ መሟገታቸውን አስታውሶ ርዕሰ አንቀጹ ጽሁፉን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG